ኢትዮጵያ በወደብ ልማትና ባህረኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት በመስጠት ግዙፍ የንግድ መርከብ ድርጅት ባለቤት ለመሆን እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በወደብ ልማትና ባህረኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት በመስጠት ግዙፍ የንግድ መርከብ ድርጅት ባለቤት ለመሆን እየሰራች ነው
ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በወደብ ልማትና ብቁ ባህረኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት በመስጠት ግዙፍ የንግድ መርከብ ድርጅት ባለቤት ለመሆን እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ።
"ብሉ ኢኮኖሚ" የዓለም አገራት የውሃ አካላትን በጋራ የሚንከባከቡበትና የሚጠቀሙበት አካሄድ ነው።
በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ሀብቱን በተሻለ መልኩ ማልማት እንዲችሉና እንዲጠቀሙ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያም ከዚህ ኢኮኖሚ ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የማሪታይም ባለሥልጣን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዓለም አቀፍ የማሪታይም ሕግ ጉዳዮች አማካሪ አነኔ ቀጄላ፤ ዘርፉ መልከ- ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ይናገራሉ።
"ብሉ ኢኮኖሚ" የማሪታይም ትራንስፖርት፣ የቱሪዝም ዘርፍ፣ የግብርና፣ ማዕድንና የውሃ ኃይልን ማዕከል አድርጎ በአንድ አገር ክልልም ውስጥ ይሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለውን የውሃ አካላት መጠቀም መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም በተለይ በማሪታይም ዘርፍ ከብሉ ኢኮኖሚ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሰች ስለመሆኗም ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ አኳያ ማሪታይም ባለሥልጣን የንግድ መርከቦችን ማጠናከርና ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
መሰል የንግድ ሥራዎች ውስጥ መሳተፍ ከባህር በር አልባነት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩ ይህ ጉዳይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
የመርከቦች ምዝገባ ማካሄድ በዚህም ተጨማሪ ገቢ ለአገሪቷ ማስገባትም በ"ብሉ ኢኮኖሚ" ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወን እንደሆነም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የወደብ ልማቶችን በስፋት ማከናወንና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርም በዋናነት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው።
በዚህ ረገድ የአገር ውስጥ ደረቅ ወደቦች ልማት ብቻ ሳይሆን የባህር በር ካላቸው አገራት ጋር በሰፊው የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሌላው የማሪታይም ባለሥልጣን በስፋት ሊሰራው ያቀደው ብቁ ባህረኞችን በስፋት ማሰልጠን እንደሆነም አክለዋል።
ይህም በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ራስን ከመቻል ባሻገር ለአገርም ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ መንገድ መሆኑንም አመላክተዋል።
"ብሉ ኢኮኖሚ" የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው።
"ብሉ ኢኮኖሚ" በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) 5 በመቶ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ዘርፉ 0 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ አስተዋጽኦ ያደርጋል።