ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ የትምህርት ተቋማት ግንባታን ለማስጀመር ሰመራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ የትምህርት ተቋማት ግንባታን ለማስጀመር ሰመራ ገብተዋል
ሰመራ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ የትምህርት ተቋማት ግንባታን ለማስጀመር አፋር ክልል ሰመራ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ ዛሬ ጠዋት ሰመራ ከተማ የሚገኘው ሱልጣን አሊ ሚራህ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደምን ጨምሮ የክልሉ አመራሮች አቀባበል አድርገዉላቸዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች አሸባሪው ህወሃት ወረራ ፈጽሞ በነበረበት ወቅት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን የመልሶ ግንባታ መርሃ ግብር ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በይፋ እንደሚያስጀምሩ ይጠበቃል።
መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በጦርነቱ በአፋር 65 ሙሉ ለሙሉ 415 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት እንደደረሳበች መግለጻቸው ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ ተቋማቱን መልሶ ለመገንባት እስከ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች ድረስ ግብረ-ህይል አቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን መስራቱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤