ቀጥታ፡

የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል---አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ሐምሌ 12/2014 (ኢዜአ) ጠንካራና የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱንና የ2015 በጀት ዓመት የድርጊት መርሃ-ግብር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች አቅርቧል።

በዚህም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና ስትራቴጂክ እቅዱን አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያግዛል ያለውን ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን ነው ያነሱት፡፡

አካታችና አሳታፊ አገራዊ ምክክር ማድረግ እንዲሁም ተቋማዊ ብቃትን ማሳደግ የስትራቴጂክ እቅዱ የትኩረት መስኮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ገለልተኝነት፣ አካታችነት፣ አሳታፊነት እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው አገራዊ ምክክር ለማድረግ እስከ 20 ሺህ የውይይት መድረኮች ሊካሄዱ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተሳታፊዎችን ልየታ ጨምሮ በተያዘው 2015 በጀት ዓመት ለሚያከናውናቸው ተግባራት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ከመንግሥት ጠይቋል።

የምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች ኮሚሽኑ ያቀረበው እቅድ አበረታች መሆኑን በመጠቆም፤ ትኩረት ሊደረግባቸውና መጨመር አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በገለልተኝነት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በሚመለከትም ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቶ በኮሚሽነሮች ምላሽ ተሰጥቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት  ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ዜጎች ግብዓት እንዲሰጡበት ሃሳብ አቅርበዋል።

መንግሥት ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ለምክክሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ሁሉም የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ለመንግስት ብቻ የሚተው ስራ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የምክክሩ ዋና ዓላማ አገርን ለማሻገር እስከሆነ ድረስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት እንዲያከናውን ምክር ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት አፈ-ጉባኤው፤ ጠንካራና የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ዜጋ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን የሚደመጡበት፣ አሸናፊ የሚሆኑበት፣ አገር የሚያጸኑበት እንዲሆን መሥራት ይጠይቃል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከምክር ቤቱ የተሰጡ ሃሳቦችን ለቀጣይ ሥራቸው በግብዓትነት እንደሚወስዱም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም