ቀጥታ፡

በታንዛንያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 66 ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ተመለሱ

ሐምሌ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በታንዛንያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 66 ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ዛሬ ተመልሰዋል።

የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የታንዛንያ ዳይሬክተር ዶክተር ቃሲም ሱፊ ዜጎቹ የተመለሱት በፈቃደኝነት መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ አስታውቀዋል።

ለኢትዮጵያውያኑ መመለስ አይኦኤም፣ በታንዛንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲና የታንዛንያ የስደተኞች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ላደረጉት ትብብርና የስዊድን መንግስት ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በተለያዩ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ስራ ከሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከናወን መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያዊያኑ የሚመለሱት ከታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ የመን እና ኦማን መሆኑንም በወቅቱ አመልክተዋል።

መንግስት በ11 ወራት በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ 102 ሺህ ዜጎችን ለመመለስ አቅዶ ከመጋቢት 27 እስከ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 51 ሺህ ዜጎችን መመለሱን አምባሳደር መለስ ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም