ኤጀንሲዎች ለጥበቃ አገልግሎት የሚያስቀጥሯቸውን ግለሰቦች ማንነት እና አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲዎች ለጥበቃ አገልግሎት የሚያስቀጥሯቸውን ግለሰቦች ማንነት እና አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀምሌ 12/2014/ኢዜአ/ ለጥበቃ አገልግሎት ዜጎችን መልምለው የሚያስቀጥሩ ኤጀንሲዎች የተቀጣሪዎቹን ማንነት እና አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን አስቀድመው ሊያረጋግጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አሳሰበ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር በከተማዋ በጥበቃ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ዜጎችን መልምለው ከሚያስቀጥሩ ኤጀንሲዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የከተማ አስተዳደሩ ክፍለ ከተሞች የፖሊስ አመራሮች በዘርፉ ያስተዋሏቸውን ችግሮች አቅርበዋል።
በዚህም ከምልመላና መረጣ ጀምሮ በርካታ ችግሮች መስተዋላቸው ተገልጿል።
ዝቅተኛ ዋጋን ፍለጋ በእድሜ የገፉና የጤና ችግር ያለባቸውን መቅጠር በስፋት መስተዋሉም ተገልጿል።
ይህም በዘርፉ ሥራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተመላክቷል።
ሐሰተኛ ዋስ፣ የሐሰት መታወቂያና ሐሰተኛ መረጃዎች በስፋት መታየቱ እና ለጥበቃ የተሰጣቸውን መሳሪያ ይዞ መጥፋት ታይቷል ተብሏል።
በተጨማሪም ኤጀንሲዎች ለጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁስ አለማሟላት እንዲሁም ግለሰቦቹ ተቀጥረው በሚጠብቁት ተቋም ላይ በርካታ ስርቆት መፈጸሙ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ፍስሐ ጋረደው እንዳሉት፤ ኤጀንሲዎች የጥበቃ አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ የተደረገው የመንግሥት የጸጥታ አካላት የማይሸፍኗቸውን ቦታዎች እንዲሸፈኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ይሁን እንጂ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በርካታ ጉድለቶች ተስተውለዋል" ያሉት ኃላፊው በቀጣይ በእውቀትና ተጠያቂነትን መሠረተ ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል።
ኤጀንሲዎች ምልመላ ሲያደርጉ በቂ ልምድ ያላቸውንና አስፈላጊውን ስነ-ምግባር ያሟሉትን መሆን እንዳለበትም አክለዋል።
ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገቡ ሥራዎችን ሊያከናውኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ቢሮው በከተማው በዚህ አገልግሎት በተሰማሩ ኤጀንሲዎች ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ጥናቱን መሠረት ያደረገ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ሰላም መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በኤጀንሲ የሚቀጠሩ ሠራተኞች አስፈላጊውን መስፈርት የሚያሟሉ፣ ለሚሰጣቸው ንብረት ኃላፊነት የሚወስዱ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አስፈላጊውን መስፈርት ሳያሟሉ በሚቀጠሩ የጥበቃ ኤጀንሲዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
የኤጀንሲ ባለቤቶችና ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ የሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመንግሥት በኩል የክትትል እና ጠንካራ መመሪያ መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል።