አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ሰብአዊ ድጋፍ እና ልማት የሚውል የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

475

ሐምሌ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ በድርቅ ሳቢያ ሊከሰት የሚችልን ረሀብ እና ሞት ለመከላከል 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አስቸኳይ ድጋፍ እንደምታደርግ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓዎር ገለጹ።

ዩኤስኤይድ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በቀጣናው በተከሰተው ያልታሰበ ድርቅ ሳቢያ ከ18 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሀብ አደጋ የተጋለጡ ሲሆን አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በተጨማሪም በሩሲያ እና ዩክሬን ቀውስ ምክንያት በአካባቢው የምግብ፣ የነዳጅ እና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በመናሩ ከባድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል።

ድጋፉ በድርቅ ምክንያት በህጻናት ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለመከላከል፣ የከብቶችን ሞት ለመቀነስ፣ የሴቶች እና ህጻናትን ጥቃት ለመከላከል፣ ለአስቸኳይ የጤና እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንደሚውል ተጠቁሟል።

ዩኤስኤይድ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን ማስፋፋት፣ ድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ እንዲሁም የማህበራዊ ጥበቃ እና ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ላይ ሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ተነግሯል።

አሜሪካ በፈረንጆቹ 2022 ብቻ 1 ነጥብ 86 ቢሊዮን ዶላር ያህል ድጋፍ ለአፍሪካ ቀንድ ያደረገች ሲሆን ከረጂዎች የተገኘው ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነው፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም