አዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ የፍጥነት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ የፍጥነት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው
ሐምሌ 12 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮ- ጂቡቲ ዋና መንገድ አካል የሆነው አዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ የፍጥነት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተጠቆመ።
ፕሮጀክቱ 60 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከ11 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንባታውን ማስጀመራቸው ይታወሳል።
መንገዱ የሚገነባው ከ6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ሲሆን በጀቱ የሚሸፈነው በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ገቢ እና ወጪ ንግድን በማሳለጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ነው የተጠቀሰው።
ግንባታውን ለማካሄድ ውል ፈጽመው ወደ ግንባታ የገቡት ጂ. ኤም. ሲ. እና ኤል. አር. ቢ. ሲ. ኤል. የተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋራጮች ናቸው።
በ ጂ. ኤም. ሲ. የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሱባረዲ ባሲረዲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ መንገዱን በ4 ዓመት ተኩል ለማጠናቀቅ ስምምነት ፈጽሞ ሥራ መጀመሩ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
ድርጅቱ ግንባታውን ከተያዘው ጊዜ አስቀድሞ በመጨረስ ለማስረከብ ለግንባታው የሚያስፈልጉትን ባለሙያዎችና መሳሪያዎች በማሟላት ሥራ መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
አስፋልቱ የሚያርፍበት መስመር መረጣ፣ ዲዛይንና መሰል ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ያስቀመጡት እቅድ መሳካቱን አክለዋል።
ይሁን እንጂ የወሰን ማስከበር ችግሮች ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የወሰን ማስከበር ችግር ካለበት ውስጥ 18 ኪሎ ሜትር ቦታ ነጻ በማድረግ እንዳስረከባቸው አስታውቀዋል፡፡
ቀሪ ቦታዎቹን ነጻ በማድረግ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አክለዋል።
ለግንባታው የሚውል ሲሚንቶ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ሌላው ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቁመው፤ አቅርቦቱ የሚጨምርበት ሁኔታዎች ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ ሱባረዲ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ መሃንዲሶችን፣ ኦፕሬተሮችን፣ ሾፌሮችንና የጉልበት ሠራተኞችን ጨምሮ ከ 550 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
የግንባታው ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ራጁማ ቱር በበኩላቸው፤ የግንባታው ጥራት አስተማማኝ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለግንባታው ጥቅም ላይ የዋሉት መሳሪያዎች የመንገዱን ጥራት ለማረጋገጥ የሚረዱ መሆኑንም በመጠቆም ግንባታውን በከፍተኛ ኃላፊነት እያካሄድን ነው ብለዋል።
ምዕራፍ አንድ የአዳማ-አዋሽ መንገድ ፕሮጀክት 34 ሜትር ስፋት ያለው፣ አራት ተሽከርካሪዎችን በግራና በቀኝ በኩል በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ ይህም የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጥ እንደሆነ ተገልጿል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ