ቀጥታ፡

ኢዜማ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገለጸ

ሐምሌ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገለጸ፡፡

ፓርቲው አዲስ የመረጣቸውን 21 የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፓርቲው መሪ፣ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ምክትል መሪ፣ ዶክተር ጫኔ ከበደ ሊቀመንበር፣ዶክተር አማኑኤል ኤርሞ፣ አቶ አበበ አካሉ ዋና ጸሓፊ እና አቶ አንድነት ሽፈራው  የፋይናንስ ሃላፊ በመሆን በጉባኤ መመረጣቸው ተገልጿል።

የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አበበ አካሉ በዚሁ ወቅት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ የአገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ  ኢዜማ  ለምክክሩ መሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።    

የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ፓርቲውን በእውቀትና በክህሎት የሚመራ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መመረጣቸውን ተናግረዋል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱም የ100 ቀናት ዕቅድ አውጥተው ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው ያነሱት፡፡

የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ኢዜማ የፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲ ለምምድን በማጠናከር በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር እየሰራ ስለመሆኑም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም