ቀጥታ፡

የዓባይ ሸለቆን በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት በዘንድሮው ክረምት 200 ሺህ ችግኞች ይተከላሉ

ሐምሌ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓባይ ሸለቆን በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት በዘንድሮው ክረምት 200 ሺህ ችግኞች እንደሚተከሉ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።

ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞች ጽድቀት መጠንም ውጤታማ እንደሆነ ገልጿል።

የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ሳይንስ ምሁራን ከበረሃማነትና ከአካባቢ መራቆት ስጋት ለመዳን የዓባይ ወንዝን ሸለቆና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮችን ወደ አረንጓዴያማነት መቀየር እንደሚገባ ይመክራሉ።

እሳቤውን ለመተግበርና የዓባይን ተፋሰስ ከአፈር መከላት ለመከላከል የዓባይ ሸለቆን በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት ተነድፎ እየተተገበረ ይገኛል።

የዓባይ ሸለቆን በቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት በኖርዌይ መንግሥት ድጋፍ በኢትዮጵያ ደን ልማት፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ገቢራዊ የሚደረግ ነው።

በስዊዲን መንግስት ድጋፍ የኢትዮጵያ ደን ልማት ደብረ ማርቆስና የሰላሌ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የሚተገበረው ፕሮጀክት በ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ግራና ቀኝ ገቢራዊ መሆን ጀምሯል።

በዚህም ተቋማቱ ችግኝ በማልማት ባሳለፍነው የ2013 ዓ.ም.ክረምት ወቅት በሰሜን ሸዋና ምስራቅ ጎጃም አጎራባች ሥፍራዎች በምርምር ተቋማቱ ብቻ ከሩብ ሚሊየን በላይ የቆላ ቀርከሃ ችግኞች ተከላ ተካሂዷል።

በዘንድሮው መርሃ-ግብርም በችግኝ ተከላው የሦስቱ ተቋማት ሠራተኞችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ባለበት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ እና ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የዓባይ ወንዝ ግራ ቀኝ ሥፍራዎች ተተክሏል።

የደን ተመራማሪው ዶክተር አደፍርስ ወርቁና በኢትዮጵያ ደን ልማት የፕሮጀክቱ ባልደረባ አቶ አዱኛው አድማስ ቀርከሃ በተለይ ለዓባይ ሸለቆ ስነ ምህዳር መጠበቅ ሁነኛ አማራጭ ነው ይላሉ።

የቆላ ቀርከሃ በዕድሜ ዘመኑ አንዴ ብቻ የሚያብብ፣ በተተከለ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ለግልጋሎት ደራሽ የሆነ፣ የተጎሳቆለ ሥነ-ምህዳር መላሽና ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቶው የበዛ መሆኑን ያነሳሉ።

ተክሉ አንዴ ከተተከለ በስሩ እየተዋለደ የሚራባ፣ በርሀ ቦታ ለይ ቅዝቀዜን የሚያመጣና ለአፈር ጥበቃ የሚመች ባህሪ እንዳለውም ይናገራሉ።

በዚህም የምርምር ተቋማት በጋራ በመሆን የተጎዳው የዓባይ ሸለቆ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ሰርቶ ማሳያ ለማድረግ ያለመ ፕሮጀከት እውን መሆን መጀሩን ገልጽው፤ ጽድቀቱም ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቆላ ቀርከሃ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ገልጸው፤ በዘንድሮው ክረምት ወቅት ብቻ 200 ሺህ ችግኞች በማፍላት በታሪክ ከፍተኛ የቀርከሃ ችግኞች ማዘጋጀት መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ተቋሙ ከያዛቸው ቁልፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የዓባይ ሸለቆ የቆላ ቀርከሃ ልማት መሆኑን አስታውሰው በልዩ ትኩረት እየሰተራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓባይ ሸለቆ ተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከል እና አርሶ አደሩም ቀርከሃ እየተከ ተጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ድጋፎች እየተገኙ መሆኑን ገልጸው፤ ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር በመደበኛ ስራነት እንዲቀጥል እንሰራለን ብለዋል።

የቀርከሃ ተክል ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ባለፈ የሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ በቀጣይነት በስፋት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር እሸቱ ወንድሙና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደምሳቸው ሽታው ችግኝ መትከልን ከደጋማ አካበጂዎች ወደብረሃማ ስፍራው ማምጣት እንደቻሉ ገልጸዋል።

የምርምር ተቋማቱ የአካባውን ማህበረስብ በግንዛቤ ፈጠራ በማስተባበር በቀርከሃ ልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከደን ልማት ተቋም ጋር በጋራ መስራታቸው ፕሮጀክቱን ውጤታማ እንዳደረገውና ለሌሎች የምርምር ተቋማት አርዓያ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀርከሃ ደን ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነች ጥናቶች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም