በተጠናቀቀው በጀት አመት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት አመት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
ሐምሌ 11 2014 (ኢዜአ ) በተጠናቀቀው በጀት አመት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣የክልሎች እና የተጠሪ ተቋማት የተጠናቀቀውን በጀት አመት የስራ አፈፃፀም እና የዘንድሮ በጀት አመትን የሚገመግም ውይይት በድሬዳዋ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት አመት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ወጭ አገራት ከተላኩት ምርቶች ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
በተለይ ሚኒስቴሩ ከክልሎች ፣ከከተማ መስተዳድሮች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥምረት በመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያስጀምረው"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አመርቂ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል።
በንቅናቄው የተዘጉ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል ፤ምርታማነት አየጨመረ መምጣቱም ተስተውሏል ነው ያሉት።
"በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከዘርፉ 5 መቶ ሚሊዮን 44ሺ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተፈጠረውን ድርቅ በመመከት ተግባራት ውስጥ የተገኘው ውጤት በዘርፉ ትልቅ ዉጤት ከተገኘበት ከ2010 ዓ/ም ከተገኘው 458 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ28 በመቶ ወይም በ110 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በአገር ውስጥ ምርትን በመተካት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማደን መቻሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ ከ2830 በላይ ከከፍተኛ እስከ አነስተኛ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ተናግረዋል ።
እነዚህ ጅምር አበረታች ተግባራት ለ255 ሺ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸው ገልፀው ይህም የዕቅድን 95 በመቶ ማሳካት ተችሏል በማለት አብራርተው አምና በተመሳሳይ ወቅት ለ172 ሺ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
የዘንድሮን የተቀናጀ ተግባራት በቁርጠኝነት በማስቀጠል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተያዘው ውጥን ማሳካት ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በስራ አፈፃፀም ግምገማ እና የዕውቅና መድረክ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በአስተዳደሩ እና በፌደራል መንግስት ቅንጅት እየተከናወኑ የሚገኙት ተግባራት የድሬደዋን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
በ1996 በተቋቋመው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር እና ከሁለት አመት በፊት አገልግሎት የጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ከአነስተኛ አስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረው የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በነገው ዕለትም በ2015 በጀት አመት ዕቅድ ላይ ውይይት የሚካሄድ እና የሚፀድቅ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት አመት የተሻለ አፈፃፀም የዕውቅና የሽልማት መረሃ ግብር ይካሄዳል።