ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እየተገኘ ያለው ድል ኢትዮጵያን ያኮራና የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና መተባበር ለዓለም ያሳየ ነው

ሐምሌ 11ቀን 2014 (ኢዜአ)በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እየተገኘ ያለው ድል ኢትዮጵያን ያኮራና የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና መተባበር ለዓለም ያሳየ መሆኑን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ገለጸ።

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወንዶች ማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ እና አትሌት ሞስነት ገረመው ለኢትዮጵያ ወርቅ እና ብር ሜዳሊያ አስገኝተዋል።

በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት ለተሰንበት ግደይ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስገኘቷ የሚታወስ ነው።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ በዓለም ሻምፒዮናው የተገኘው ድል የኢትዮጵያን ሕዝብ ያኮራ ነው ብሏል።

በውድድሩ የታየው የቡድን ሥራና የአትሌቶች እርስ በርስ መተባበርና አንድነት ደግሞ ከምንም በላይ አስደሳች ነበር ብሏል።

''በተለይ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ታምራት ቶላ ሁለተኛ የወጣውን የሀገሩን ልጅ አትሌት ሞስነት ገረመውን የተቀበለበትና ያቀፈበት መንገድ ስመለከት በደስታ ስሜት እንባ ተናንቆኝ ነበር'' ነው ያለው።

በዚህ የወንዶች ማራቶን ሌላኛው ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው የቤልጂየም አትሌት ተቃቅፈው የነበሩትን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተቀላቅሎ ደስታውን አብሮ ሲገልጽ መመልከትም ያስደስታል።

ይህ ውድድር እኛ እርስ በርስ ከተከባበርንና ከተዋደድን ሌላው እንደሚያከብረን፣ እንደሚያቅፈን አመላካች መሆኑንም ጠቅሷል።

በተመሳሳይ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ለተሰንበት ግደይ እና አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ያሳዩት አንድነትና ስሜት አስደሳች ነበር ነው ያለው።

ኢትዮጵያዊያኑ ድል ባደረጉት በሁለቱም ውድድር የቡድን ሥራ እንደነበረው አስታውሶ፤ይህ በቀጣይም መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጸው።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት ድህነትን ታግሎ መጣል ቀዳሚው ሥራ አድርጎ ከተነሳ ታላቋን ኢትዮጵያ መገንባት ይቻላል ብሏል።

የዓለም ሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደሰተና የአንድነት ስሜት የፈጠረ እንደሆነ ነው የተናገረው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም