ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ዙሪያ ዛሬ ይወያያል

ሐምሌ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ዙሪያ ዛሬ ውይይት ያደርጋል።

ኮሚቴው ውይይቱን የሚያደርገው ኢትዮጵያ አበዳሪዎች የብድር ማስተካከያ እንዲያደርጉ ያቀረበችን ጥያቄ ተከትሎ ነው።

የእዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ መወሰድ ባለባቸው የፋይናንስ እርምጃዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ዘጠነኛው የፓሪስ ፎረም ከሰሞኑ መካሄዱ ይታወቃል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ አበዳሪዎች የቡድን 20 የብድር ማገገሚያ የጋራ ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ የእዳ እፎይታውን መቼ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በግልጽ ማሳወቅና ማዕቀፉን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው ነበር።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ላይ ዛሬ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

የቡድኑ አባል አገራት እና የፓሪስ አበዳሪዎች ክለብ እ.አ.አ 2020 ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት እ.አ.አ መስከረም ወር 2021 የኢትዮጵያን የእዳ እፎይታ ጥያቄ የሚመለከት ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል።

ፈረንሳይ እና ቻይና የአበዳሪዎቹን ኮሚቴ በሊቀመንበርነት የሚመሩ አገራት ናቸው።

ኮሚቴው እ.አ.አ በመስከረም ወር 2022 በብድር ማስተካከያ ላይ ውይይት አድርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ተጨባጭ ውሳኔዎችን ሳያሳልፍ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም