ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ ከ2 ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል ጀመረ

ሆሳዕና ሐምሌ 11/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከ2 ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መግባቱን ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሰራተኞች በደቡብ ክልል ካምባታ ጣምባሮ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ማቲኦባ ተፋሰስ ላይ የችግኝ ተከላ መርሐግብር እያካሄዱ ነው።

የኢንቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር መለስ ማርዮ ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ከመጀመሩ በፊት በየአመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደ ሀገር ይተክል እንደነበር አስታውሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ እንደሀገር በንቅናቄ ከተጀመረም በኋላ ዘርፉን ሲደግፍ መቆየቱን አብራርተዋል።

በዘንድሮውም ዓመት ለ4ኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትግበራ ከ2 ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱን አስረድተዋል።

ዛሬ ኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሰራተኞች በከንባታ ጠምባሮ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ ማቲኦባ ተፋሰስ በመገኘት የዕቅዱ አካል የሆነውን 3 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞች ተከላ መርሐ ግብር እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ስራተኞችና የአካባቢው የማህበረሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በመቀጠልም በደቡብ ክልል በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ የሚገኘውን የኢንስቲትዩቱ የችግኝ ማፊያ ጣቢያ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም