ተመራቂ ተማሪዎች ሙያቸውን ወደ ተግባር በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች ሙያቸውን ወደ ተግባር በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል
ሀምሌ 10/2014/ኢዜአ/ ተመራቂ ተማሪዎች ሙያቸውን ወደ ተግባር በመቀየር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ኮተቤ የትምህርት ዩንቨርሲቲ በተለያዪ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 891 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡
በመርኃግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አባዱላ ገመዳና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የትምህርት ሚንስትሩ በዚሁ ወቅት የትምህርት ጥራት ጉድለትን ለመቅረፍ ትውልድን የሚቀርፁ ብቁ መምህራንን ማፍራት ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
መምህራን ለተማሪዎቻቸው በእውቀትና በመልካም ስነ ምግባር አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ በቂ እውቀት ተላብሰው ተወዳዳሪ እና ብቁ ትውልድን መፍጠር የሚችሉ መምህራን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት፡፡
ከዚህ አኳያ ተመራቂ ተማሪዎች ሙያቸውን ወደ ተግባር በመቀየር ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ትልቅ አደራ እንደተጣለባቸውም ተናግረዋል ፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነ መስቀል ጠና በበኩላቸው ዩንቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 1 ሺህ 482 ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች ራሳቸውን በእውቀት በማጎልበት ለቀጣይ የትምህርት ምእራፍ እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምሩቃን ነገሮችን በስሜት ሳይሆን በእውቅት በመረዳት ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በታማኝነት እና በቅንነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል፡፡
በጤና ሳይንስ ዘርፍ 3 ነጥብ 97 በማምጣት በከፍተኛ ማእረግ የተመረቀችው ነቢያት አስራት ለዚህ የበቃችው የትምህርት ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀሟ መሆኑን ተናግራለች ፡፡
በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸውን ዓላማ እና ግብ ሊያስቀምጡ እንደሚገባ መክራለች፡፡
በ "አርባን ኤንድ ሪጅናል ፕላኒንግ" ትምህርት መስክ 3 ነጥብ 81 በማምጣት የማእረግ ተመራቂ የሆነው ብርሃነ አማረ ለዚህ ክብር እስከሚበቃ ድረስ የበርካታ ሰዎች ድጋፍና አስተዋጽኦ እንዳልተለየው ተናግሯል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች ለዚህ ያበቃንን ህዝብ በታማኝነት እና በቅንነት ማገልገል ሀገራዊ ግዴታችን ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
ዩንቨርሲቲው ያስመረቃቸው ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የስልጠና መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸውም በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡