በየአካባቢው ሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታ የሚያካሂዱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው-የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በየአካባቢው ሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታ የሚያካሂዱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው-የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር

ሐምሌ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በየአካባቢው ሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታ የሚያካሂዱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ላለፉት 60 ዓመታት በተለያዩ የሎተሪ አማራጮች የዕድል ጨዋታ ለሕብረተሰቡ ሲያቀርብ ቆይቷል።
በተለይ የወረቀት ሎተሪ ተብለው የሚታወቁት መደበኛ፣እንቁጣጣሽ፣ እድል፣ልዩ፣ የገና ስጦታ፣ ትንሳኤ፣ቶምቦላ እና ዝሆን ሎተሪ በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በቅርቡም "አድማስ ሎተሪ" የተሰኘ የዲጂታል ሎተሪ ቲኬት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡
አስተዳደሩ በብቸኝነት የገንዘብ ሎተሪ ለማካሄድ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም በየአካባቢው የተለያዩ ዕጣዎችን በማዞር ሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታን የሚያጫውቱ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ነዋይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አስተዳደሩ የገንዘብ ሎተሪ የማካሄድና ፈቃድ የመስጠት ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም አስተዳደሩ የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎችን ጨምሮ ለማህበረሰብ አገልግሎት ለሚውሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ፤ በመዝናኛ ስፍራዎች ለሚካሄድ መደበኛ የቢንጎ ጨዋታ እንዲሁም ለስፖርት ውርርዶች ሎተሪዎች ፈቃድ መስጠቱን አንስተዋል፡፡
ሆኖም በየአካባቢው የተለያዩ ዕጣዎችን የሚያዞሩና በሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታ የተሰማሩ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሕገ-ወጥ የዕድል ጨዋታ ከግሮሰሪ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሆቴሎች የሚካሄድ እንዲሁም ትንንሽ ጣሳ ይዞ ዕጣ ከማውጣት እስከ ሞባይል የረቀቀ ሕገ-ወጥ ተግባር የሚካሄድበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ይህን ሕገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ከፖሊስ ጋር ዘመቻ በማካሄድ በርካቶችን ለፍርድ በማቅረብ በገንዘብና እስር እንዲቀጡ መደረጉንም ለአብነት አንስተዋል።
በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር መመሪያ መሠረት ሕገ-ወጥ የእድል ጨዋታ በሚያከናውኑ አካላት ላይ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት እሥራትና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚያስጥል ተደንግጓል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ