ቀጥታ፡

በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ ህብረት አስፈፃሚ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

ሐምሌ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት የአባል ሃገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት የህብረቱ 41ኛው የአስፈፃሚ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በመደበኛ ስብሰባው ተሳትፏል።

የአስፈፃሚ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት የ2023 በጀት 654 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ያጸደቀ ሲሆን 67 በመቶ የሚሆነው በአጋሮች የሚሸፈን እንደሚሆን ታውቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበጀት ማፅደቁ ሂደት ለሰላም ማስከበር የሚውለው በጀት ሙሉ በሙሉ በአለም አቀፍ አጋሮች እንዲሸፈን መደረጉ አግባብ አለመሆኑን አንስተዋል።

ቁልፍ ለሆነው የሰላም ጉዳይ ከሚውለው በጀት በቀጣይ ቢያንስ አብላጫውን አህጉሪቱ በራሷ መሸፈን እንዳለባት አቶ ደመቀ ያስገነዘቡ ሲሆን ሃሳቡን ሌሎች ሃገራትም ደግፈውታል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል የአለም አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ሆና እንድታገልገል በመደበኛ ስብሰባው በእጩነት የቀረበች ሲሆን ፤ ምክር ቤቱ እጩነቷን በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል።

በውክልናው ከኢትዮጵያ ጋርም ሌሎች ሶስት ሃገራትም ተካተዋል።

የአፍሪካ የህብት ሪፎርምን አመልክቶ የአስፈፃሚ ምክር ቤቱ የህብረቱን የሰራተኞች አስተዳደርን በስፋት ተመልክቶታል።

በዚህም አብዛኛው የህብረቱ ሰራተኞች በጊዜያዊ ኮንትራት የተቀጠሩ መሆኑ ተጠቅሶ ይህ መቀየር እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።

ምክር ቤቱ ረጅም አመት በጊዜያዊ ቅጥር የሰሩ የተቋሙ ሰራተኞች የብቃት መመዘኛ ተፈትነው አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉ በሙሉ ወደ ቋሚ ሰራተኛነት እንዲሸጋገሩ ወስኗል።

በቅርቡ ለተመሰረተው የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናጋጅ ሃገር መምረጥ የ41ኛው የህብረቱ የአስፈፃሚ ምክር ቤት ሌላው አጀንዳ የነበረ ሲሆን በድምፅ ብልጫ ርዋንዳ የኤጀንሲው መቀመጫ ሆና ተመርጣለች።

የአፍሪካ መድህኒቶች ኤጀንሲ በአፍሪካ የሚመረቱ መድሃኒቶች እና የህክምና መርጃ መሳሪዎችን ደረጃ የሚመድብ እና ፈቃድ የሚሰጥ ተቋም እንደሚሆን ይጠበቃል።

መደበኛ ስብሰባው የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ራሱን ችሎ ሙሉ ስልጣን እንዲኖረው የመመስረቻ ሰነዱ ላይ የቀረበውን ረቂቅ ማሻሻያ አፅድቋል።

ማሻሻያው በአህጉሪቱ ወረርሽኞች ሲከሰቱ አፍሪካ ሲዲሲ ከአለም ጤና ድርጅት እና አባል ሃገራት ጋር በመግባባት እንዲያውጅ ስልጣን የሚሰጠው ይሆናል።

በ41ኛው የአፍሪካ ህብረት አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተሳተፈው ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም