በዘንድሮው ክረምት በዓባይ ሸለቆ በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት 200 ሺህ ችግኞች ይተከላሉ-የኢትዮጵያ ደን ልማት - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው ክረምት በዓባይ ሸለቆ በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት 200 ሺህ ችግኞች ይተከላሉ-የኢትዮጵያ ደን ልማት
ሐምሌ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በዘንድሮው ክረምት በዓባይ ሸለቆ በቆላ ቀርከሃ የማልማት ፕሮጀክት 200 ሺህ ችግኞች እንደሚተከሉ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።
በፕሮጀክቱ ሁለተኛው ዙር የቆላ ቀርቀሐ ችግኝ ተከላ ዛሬ ተካሂዷል።
የዐባይ ሸለቆን ቀርከሐ የማልማት ፕሮጀክት በስውዲን መንግስት ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ ደን ልማት፣በሰላሌ ዩኒቨርስቲና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲዎች ትብብር ገቢራዊ የሚደረግ ነው።
በዚህም ተቋማቱ ችግኝ በማልማት ባሳለፍነው የ2013 ክረምት ወቅት በሰሜን ሸዋና ምስራቅ ጎጃም አጎራባች ስፍራዎች በምርምር ተቋማቱ ብቻ ከሩብ ሚሊየን በላይ የቆላ ቀርከሐ ችግኞች ተከላ ተካሂዷል።
በዘንድሮው መርሐግብርም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጃርሶ ግራር እና ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ በሚገኙ የዐባይ ወንዝ ግራ ቀኝ ስፍራዎች መተከል ተጀምሯል።
በችግኝ ተከላው የሶስቱ ተቋማት ሰራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ተቋሙ ከያዛቸው ቁልፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የዓባይ ሸለቆ የቆላ ቀርከሐ መሆኑን ገልፀዋል።
የቀርቀሐ ተክል ከአካባቢው ስነ ምህዳር ባለፈ የሚኖረው ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፣ፕሮጀክቱ በቀጣይነት በስፋት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከደን ልማት ተቋም ጋር በጋራ ገቢራዊ መደረጉ ውጤታማ እንዳደረገውና ለሌሎች ተፋሰሶች የምርምር ተቋማት አርዓያ እንደሆነ የተቋማቱ ተወካዮች ገልፀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ የቆላ ቀርከሐ ለተራቆተው የዓባይ ሸለቆ ስነ ምህዳር ጥበቃና ለሕዳሴው ግድብ ከደለል መሞላት ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ገልፀዋል።
በዘንድሮው ክረምት ወቅት ብቻ 200 ሺህ ችግኞች በማፍላት በታሪክ ከፍተኛ የቀርከሐ ችግኞች ማዘጋጀት መቻሉን ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት ጀምሮ ገቢራዊ መሆን የጀመረው ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በቀርከሐ ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነች ጥናቶች ያመላክታሉ።