በክልሉ ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል

94

ባህር ዳር (ኢዜአ )ሐምሌ 9/2014  በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ከ42 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ማምሻውን ተጀምሯል።  

በቢሮው የገቢ ዕቅድና ጥናት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አትንኩት በላይ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትን ማፋጠን ይገባል።

በዚህም በአዲሱ በጀት ዓመት ከ42 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከታቀደው ገቢ ውስጥ ከ38 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው መደበኛ ገቢ ሲሆን ቀሪው ከ4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ደግሞ ከከተማ አገልግሎት እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የዘንድሮው ዕቅድ ካለፈው ዓመት ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር ከ43 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለተፈጻሚነቱም በየደረጃው ያለው አመራር እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

"ይህን የገቢ ዕቅድ ለማሳካትም በሁሉም ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ህዝቡን ያሳተፈ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ይገባል" ሲሉም አስግንዝበዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ሃላፊዎች ተሳትፈዋል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም