ከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያስገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያስገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት አስረከበ
ሐምሌ 09 ቀን 2014(ኢዜአ) አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያስገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት አስረከበ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ላለቸው ግለሰቦች ቤቱን ያስረከቡት ።
በከተማ አስተዳደሩ የተገነቡት እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንደሆኑም ተጠቁሟል።
አስተዳደሩ የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ሕብረተሰቡን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት የተናገሩት።
የከተማ ቤቶችን ችግር ለማቃለል በመንግስት ብቻ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው ባለሀብቶች በስፋት የሚሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም አዳዲስ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው ክፍለ ከተማው መሰል ስራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
ክፍለ ከተማው በርካታ በዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም በመተጋገዝና በመተሳሰብ ችግረኞችን የማገዝ ስራ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የጋራ መኖሪያ ቤት ከተረከቡ ነዋሪዎች መካከል አቶ አሸናፊ ደምሴ እና ወይዘሮ ዘነበች ዘገየ፤ በፊት የነበሩበት ቤት የፈራረሰና ክረምት በመጣ ቁጥር በጣም ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች አንድ መጸዳጃ ቤት በጋራ ስለሚጠቀሙ ለተለያዩ በሽታዎች ይዳረጉ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ያስረከባቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ህይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ተስፋ አድርገዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቱ ባለ አራት ወለል ህንጻ ሲሆን ባለአንድና ባለሁለት መኝታ ክፍሎች ያሉት እንደሆነም ተገልጿል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን የገነባው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑም ታውቋል።