ቀጥታ፡

ምሩቃን በሰለጠኑበት መስክ ሀገራቸውን በቅንነት ሊያገለግሉ ይገባል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

ባህርዳር ሐምሌ 9/2014 (ኢዜአ) ምሩቃን በሰለጠኑበት መስክ ሀገራቸውን በቅንነት ለማገልገል ችግሮችን በጥናትና ምርምር መፍታት እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስገነዘቡ።

የአማራ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ለ2ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 73 ተማሪዎች በ2ኛ ዲግሪ ዛሬ አስመርቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በምረቃ ፕሮግራሙ እንደተናገሩት ሀገሪቱን ከውስብስብ ችግሮች ለማላቀቅና ዕድገቷን ለማፋጠን የሚያጋጥሟትን ችግሮች በጥናትና ምርምር ለይቶ መፍታት የሚቻለው በቂ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው።

የተማረ የሰው ኃይል የሌላቸው ሀገሮች በችግር የተተበተቡ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ እኛም ከዚህ ችግር ለመውጣት የተማረ የሰው ኃይልን በብዛትና በጥራት ለማፍራተ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ትምህርት የችግር መፍቻ መሳሪያ መሆኑን መንግስት ተገንዝቦ ዘርፉን ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ከሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ ስራ ይቀረናል ብለዋል ።

በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ምሩቃን በየተመደቡበት የስራ መስክ የህዝብን አንገብጋቢ ችግር ቅድሚያ ሰጥተው መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

ለዚህም ምሩቃን መልካም ሰብዕናን በመላበስ አሁናዊ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየርና ተገልጋዩን ህብረተሰብ በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል የራሳችሁን አሻራ ልታኖሩ ይገባል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱም የህዝብን እርካታን ለመፍጠር ከረጅም ጊዜ ስልጠና ባሻገር በሚሰጣቸው አጫጭር ስልጠናዎች የመንግስት ሰራተኞችንና የግሉን ዘርፍ አቅም ለመገንባት የጀመረውን ስራ በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስትም ለተቋሙ ለሚያደርገው የስራ እንቅስቀቃሴ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት አቶ እሱባለው መሰለ በበኩላቸው ተቋሙ ከክልሉ መንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚችል ዓመራርና ባለሙያን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ራስን ማልማትና ማብቃት ከተቻለ ዘላቂ ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል የጠቀሱት አቶ እሱባለው ይህ እንዲረጋገጥም ተቋሙ ከመቸውም ጊዜ በላይ የሰው ኃብት ልማቱ ላይ የጀመረውን ስራ ይበልጥ እንደሚያጠናክርም አስረድተዋል።

ተቋሙም ላለፉት ሁለት ዓመታት በፐብሊክ ፖሊሲ ኤንድ ሊደርሽፕ፣ በፒስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና በፖለቲካል ኢኮኖሚ ለ2ኛ ዙር በ2ኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 73 ተማሪዎችን ማስመረቁንም ጠቁመዋል።

በተማርኩት የትምህርት ዘርፍ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግና የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ በሰላምና ልማት የተመረቁት ወይዘሮ ያልጋ ገብረስላሴ ናቸው።

የሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥም የራሴን ድርሻ ለማበርከት ከመቸውም ጊዜ በላይ ህዝቤን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል።

ከምረቃ ስነስርዓቱ ጎን ለጎን የተቋሙ 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል የተከበረ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም