ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት አስረከቡ

ሐምሌ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤት አስረከቡ።

የኢትዮጵያ ኮንሥትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለ አራት ፎቅ 29 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ገንብቷል ።

ከቤቶቹ መካከልም 19 ቤቶች የጋራ መኖሪያ ህንጻው በተገነባበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች መተላለፉ ተጠቁሟል።

በከተማዋ ያለውን የቤት ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ቤቱን ገንብቶ ላስረከበው የኢትዮጵያ ኮንሥትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምስጋና አቅርበዋል።

የአቅመ ደካሞችን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት ተቋማትንና ባለሃብቱን በማስተባበር ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሐመድ በክፍለ ከተማው በርካታ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ሌሎቹ ተመሳሳይ ሥራዎችን በመሥራት ለነዋሪው ተጠቃሚነት አንደሚሠራ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም