በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ፈጥኖ መድረስ የሚችል የሰለጠነና የዘመነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መፍጠር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ፈጥኖ መድረስ የሚችል የሰለጠነና የዘመነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መፍጠር ይገባል
ሐምሌ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ፈጥኖ መድረስ የሚችል የሰለጠነና የዘመነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መፍጠር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የበላይ ጠባቂ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር 19ኛ ብሔራዊ ጠቅላላ ጉባኤውን የማኀበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ''የውስጥ አቅም ማጎልበት እና በእጃችን ያሉ ሃብቶችን በማልማት ሰብአዊ ተደራሽነትን ማሳደግ ይገባል''።
ባለፋት ሶስት አመታት ሕዝብና አገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበረና ከዚህም ለመውጣት የጋራ ትግል የተደረገበት ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህ ጉዞ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የዜጎችን ህይወት በመታደግ፣ የተከፉትን እና ልባቸው የተሰበረ ቤተሰቦችን በማገዝ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
ለዚህም ተግባሩ ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን 23ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፌዴሬሽኑን ከፍተኛ ሽልማት ለመሸለም መብቃቱንም አስታውስዋል።
በተጨማሪም ማሕበሩ የአስተዳደር ቦርድ (govering board) አባል አድርጎ በድጋሚ መመረጡንም ተናግረው ይህ መሆኑ ማሕበሩን ለበለጠ ስራ የሚያበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል።
በማሕበሩ አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ለመድረስ ያሳዩትና አሁንም የሚያደርጉት ወገን ለወገን መረዳዳት ትልቅ ምስክር ነው ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ ወደ ፊት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ለቶጎጂ ወገኖች ፈጥኖ መድረስ የሚችል የሰለጠነና የዘመነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊኖር ይገባል።
በተጨማሪም የውስጥ አቅም ማጎልበት እና በእጅ ያሉ ሃብቶችን በማልማት ሰብአዊ ተደራሽነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
በጉባዔው የብሔራዊ አስተዳደር ቦርድ ምርጫ፣ የጽህፈት ቤቱ የአራት አመት የክንውን ሪፖርትና ሌሎች የማኀበሩ ስራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ኢትዮጵያዊያንን፣ የአለም ማህበረሰብና አጋሮችን በማስተባበር ወቅቱን የጠበቀ፣ ተገቢ የሰብዓዊና የልማት ሥራዎችን የሚተገብር መሆኑም ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም የአደጋ ተጋላጮችን መከራና ስቃይ በመከላከል እና በማቃለል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ነው የተባለው።