ቀጥታ፡

ቋሚ ኮሚቴው የከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቀነስ ጥናትን መሰረት ያደረገ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ያካሄዳል

ሀምሌ 8/2014/ኢዜአ/ የከተማ ቤቶች ግንባታ፣ የትራንስፖርት ዘርፍና ከተሞች ላይ የሚስተዋል የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ ጥናትን መሰረት ያደረገ የክትትልና ቁጥጥር ሥራን እንደሚያካሂድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የከተሞች መልካም አስተዳደር፣ ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ግንባታ እና የትራንስፖርት አስተዳደር ሥርዓትን መዳሰስ የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወያይቷል።

ኮሚቴው ከአዲስ አበባ እና ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲዎቹ የምህንድስና እና የመልካም አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ ከተሞችን የመልካም አስተዳደር ሁኔታ፣ ወጪ ቆጣቢ የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ፣ የዲዛይን እና ኮንስትራክሽን ዕቃዎች እንዲሁም በትራንስፖርት ሥርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት ለመጠቀም ጥናትን መሰረት ያደረገ ሳይንሳዊ የክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ሥራ ማከናወንም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተነስቷል።

በከተሞች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስም ከትምህርት ተቋማቱ ጋር የሚካሄደው ጥናት የሕዝብን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ ምክር ቤቱ ሕግ ማውጣት፣ ክትትልና ቁጥጥር ማካሄድ፣ የፓርላማ ዲፕሎማሲና የሕዝብ ውክልና የሚሉትን ኃላፊነቶች ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  

በአስፈጻሚና ተጠሪ ተቋማት የሚካሄድ ክትትልና ቁጥጥር ሥራም ዜጎች የሚገጥሟቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቀነስ ጥናትና ምርምር ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ እና ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚካሄዱ ጥናቶችም በከተሞች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቀነስ ሳይንሳዊ ምላሽ የሚያገኙበትን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለማካሄድ እንደሚረዳ አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹም የከተማ መልካም አስተዳደር፣ ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ግንባታ እና የትራንስፖርት አስተዳደር ሥርዓቱን የሚዳስሱ ጥናቶች ለማካሄድ መስማማታቸውን አድንቀዋል።

በጥናት ግኝቱ የሚቀርቡ ምክረ-ሃሳቦችን መሰረት በማድረግም የዜጎች ተጠቃሚነት ውጤት የሚያመጣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚያካሄድ አስታውቀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር እሸቱ ተመስገን፤ በጥናቱ የሚገኙ ተሞክሮዎች ለኢትዮጵያ ልማት አዎንታዊ ውጤት እንዲያመጡ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በከተሞች ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የትራንስፖርት ዘርፉን ማሻሻል በሚቻልባቸው ዘርፎች ላይ ጥናቱ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

በቀጣይም ጥናቱን መሰረት በማድረግ አስፈጻሚና ተጠሪ ተቋማት ላይ ውጤታማ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚካሄድ አንስተዋል።

የዩኒቨርሲቲዎቹ የሥራ ኃላፊዎችም ቋሚ ኮሚቴው በከተሞች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሳይንሳዊ የምርምር ዘዴ ለመመለስ ማሰባቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚያካሂዷቸው የምርምር ሥራዎችም ችግር ፈቺና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የጥናት ውጤቶቹም በአስፈጻሚና ተጠሪ ተቋማት ላይ የሚካሄዱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን ስኬታማ እንደሚደርግ ገልጸዋል።

የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪ ተቋማቶቻቸው ላይ የክትትል፣ የድጋፍና የቁጥጥር ሥራን እያካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም