የዲጂታል ሎተሪ ትኬት አገልግሎት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ሎተሪ ትኬት አገልግሎት ሊጀመር ነው
ሐምሌ 08 ቀን (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሎተሪ አገልግሎት “አድማስ ሎተሪ” የተሰኘ የዲጂታል ሎተሪ ትኬት አገልግሎት ሊጀምር ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም የሎተሪ ትኬት በዲጂታል አማራጭ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩና የሎተሪ አገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ ፈርመዋል።
አድማስ ሎተሪ የተሰኘው የዲጂታል ሎተሪ አገልግሎት በአጭር የጽሁፍ መልዕክት 605 እና በቴሌብር *127# የዲጂታል ትኬት አገልግሎቱ መቅረቡን ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አገልግሎቱ ተደራሽነትን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
የዲጂታል ስርዓትን እንገነባለን ስንል በሁሉም ዘርፍ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ማህበረሰቡ ባለበት ሆኖ የተለያዩ አገልግሎቶችን በኦንላይን አማራጭ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ በበኩላቸው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር አብረን በመስራትና የተሻለ ስራን በማከናወን ለኢትዮጵያ እድገት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
“አድማስ ሎተሪ” የኢትዮጵያ የሎተሪ አገልግሎት እ.አ.አ በ2022 በቴክኖሎጂ የዘመነ የእድል ጨዋታዎችን ለማስፋፋት የያዘውን ራዕይ ለማሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የዲጂታል አገልግሎቱ ተደራሽነት የሚያሰፋና ወጪን የሚቆጥብ ነው ተብሏል።