የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሠራተኞች በአፈር መሸርሸር የሚጎዱ መንገዶችን ለመታደግ በሚያስችል ሁኔታ ችግኝ እየተከሉነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሠራተኞች በአፈር መሸርሸር የሚጎዱ መንገዶችን ለመታደግ በሚያስችል ሁኔታ ችግኝ እየተከሉነው
ሐምሌ 8/2014 (ኢዜአ) በአፈር መሸርሸር የሚጎዱ መንገዶችን ለመታደግ በሚያስችል ሁኔታ ችግኝ ተከላ እያከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሠራተኞች ተናገሩ፡፡
የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች እስከሚቀጥለው ወር አጋማሽ 1 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅዳቸውን ዛሬ ጀምረዋል።
የተቋሙ የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞችም በአፍሪካ ልህቀት ማዕከል አካባቢ በዛሬው እለት 2ሺህ ችግኞችን ተክለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የአካባቢ፣ ማህበራዊና የሥራ ቦታ ደኅንነት ዳይሬክተር ገነት አለማየሁ እንዳሉት፤ የተቋሙ ሠራተኞች በአፈር መሸርሸር የሚጎዱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመታደግ በሚያስችል ሁኔታ ችግኝ እየተከልን ነው ብለዋል።
በአገሪቱ ከፍተኛ የንግድና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ የሚረዱ መንገዶች በአፈር መሸርሸር ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል።
ይህንን ችግር በሚያስተካክል አግባብ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተቋሙ ሠራተኞች ችግኝ እየተከሉ መሆኑን አብራርተዋል።
በአፍሪካ ልህቀት ማዕከል አካባቢ በተካሄደ የችግኝ ተከላ ከ200 በላይ የሚሆኑ የዋናው መሥሪያ ቤት አመራርና ሠራተኞች ተሳትፈዋል ብለዋል።
የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ችግኝ መትከልን እኛ ኢትዮጵያዊያን በኃላፊነት ከምናከናውናቸው አብይ ተግባራት መካከል አንዱ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚሰራባቸው አካባቢዎች መሰል ችግኝ ተከላ እየተከናወነ ይገኛልም ሲሉ አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየገነባች ላለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት የውሀ እጥረት እንዳያጋጥምና የአገሪቱን የተዛባ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ችግኝ መትከል ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ተቋሙ በቀጣይ ችግኝ በተተከለባቸው ቦታዎች በመገኘት የመንከባከብ ሥራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደጀኔ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ የአገሪቱን ሕዝብ የመኖር ዋስትና ከምናረጋግጥበት ተግባራት መካከል ምቹ የአየር ሁኔታንም መፍጠር አንዱ መሆኑን በመረዳት ችግኝ ልንተክል ይገባል ብለዋል፡፡
ዛፍ መትከልና አካባቢን መጠበቅ የትርፍ ጊዜ ሥራ ሳይሆን የህልውና ሥራ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአገር ደረጃ ለአራተኛ ዙር እየተካሄደ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ተሳታፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት የተቋሙ ሠራተኛ ወይዘሮ ሐዳስ ኪዳኔ ናቸው፡፡
ችግኝ መትከል ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመጥቀስ፤ ለአብነትም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለሰው ልጆች ተስማሚና ንጹህ አየር ለማስገኘት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡