ቀጥታ፡

መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ፊንላንድ ትደግፋለች

ሐምሌ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ ፊንላንድ እንደምትደግፍ የአገሪቱ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ልዩ ተወካይ ሱልዳን ሰዒድ አህመድ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ከልዩ ተወካዩና በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኦቲ ሆሎፖይነን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው የሁለቱ ሀገራት ፓርላማ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

ዶክተር ዲማ ለፊንላንድ ፓርላማ ልዩ ተወካይና አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን ብትችለም በሂደቱ ደግሞ የተለያዩ ፈተናዎች ነበሩ ብለዋል።

በተለይ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የሰላም አማራጭን ተከትሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ፊንላንድ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንድትደግፍ ጠይቀዋል።

የፊንላንድ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ልዩ ተወካይ ሱልዳን ሰዒድ አህመድ በበኩላቸው አገራቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ ሰላምን ማምጣት አላማ ያደረገውን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ፊንላንድ ትደግፋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው መሪነቷን ለማስጠበቅ የራሷን ሰላም መጠበቅ እንደሚኖርባት አመልክተዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ በየብስና በአየር ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ በድጋሚ መጀመሩ ፊንላንድ እንደምታደንቅ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ፊንላንድ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አክለዋል።

የፊንላንድ ፓርላማ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም የ29 ዓመቱ ትውልደ-ሶማሊያዊውን ሱልዳን ሰዒድ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰላምን የማምጣት ሂደት እንዲደግፉ በማለም ልዩ ተወካይ አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ነው።

የልዩ ተወካዩ መሾም ፊንላንድ በቀጠናው ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም