ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን የአረንጓዴ ልማትን እየተገበረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን የአረንጓዴ ልማትን እየተገበረች ነው
ሐምሌ 08/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በምሳሌነት እያከናወኑ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ዕድገት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በምሳሌነት እያከናወኑ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ስትሆን ይህንንም ለዓለም በተግባር እያስመሰከረች መሆኗን ነው ዶክተር ገመዶ ዳሌ የተናገሩት።
መገናኛ ብዙኃን በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ያላቸውን የዘገባ ሚና ለማጠናከር ያለመ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።
ዶክተር ገመዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አደጋ የደቀነውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ውጤት እያስመዘገበ ነው።
ኢትዮጵያ በፖሊሲዎቿ ጭምር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን በመቅረፅ እየሠራች መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዓለምአቀፋዊ መድረኮች የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመከላከል ርብርብ እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ከሶስት ዓመታት በፊት የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ሀገሪቱ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ምሳሌ የሚያደርጋትን የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማትም እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው መገናኛ ብዙሃኑ ይህንን ጥረት በአግባቡ በመዘገብ ህዝቡም ጥረቱን እንዲያጠናክር ማስገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን በዕውቀት ላይ ተመሥርተው መዘገብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ልማት አዘጋገብ የሥራ መመሪያ መዘጋጀት አለበት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንም ለመመሪያው ዕውን መሆን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ልማት ዓመቱን በሙሉ የሚከናወንና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ በየአካባቢው ካሉ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች እስከ ዲጂታል ሚዲያው ድረስ የአየር ንብረት ለውጥንና የአረንጓዴ ልማት ሥራን በየዕለቱ መዘገብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የባለሙያዎችን የአዘጋገብ አቅም ለማሳደግና በዕወቀት ላይ የተመሠረተ ዘገባ እንዲያደርሱ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
መድረኩ በመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና በዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ዕድገት ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ሲሆን ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የመጡ ጋዜጠኞች እየተሳተፉ ነው።