በደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳ ወደ ተሟላ ሰላም መመለሱን ነዋሪዎች እና የወረዳዋ አስተዳደር አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳ ወደ ተሟላ ሰላም መመለሱን ነዋሪዎች እና የወረዳዋ አስተዳደር አስታወቁ
አርባ ምንጭ ሐምሌ 8/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ችግር ውስጥ የነበረው የሰላም ሁኔታ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን የወረዳው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳደር አስታወቁ።
በልዩ ወረዳው የአርጉባ ቀበሌ ነዋሪና የአገር ሽማግሌ ግርቴ ገሌቦ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፈው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ የመዋቅር ጥያቄን ተከትሎ በወረዳው ግጭት ተነስቶ ነበር።
ያለአግባብ ተከስቶ በነበረው ግጭትም በህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።
"ማንኛውንም ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እየተቻለ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈፀም የተደረገው ሙከራ የአካባቢውን ሰላም ከማናጋት ባለፈ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሶ አልፏል" ብለዋል።
ተከስቶ ለነበረው የፀጥታ መደፍረስ እጃቸው አለበት በሚል የተጠረጠሩ አካላትን ለህግ አሳልፎ ከመስጠት ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲመጣ ከኮማንድ ፖስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑንም አቶ ግርቴ አስታውቀዋል።
ከልዩ ወረዳው የሃይማኖት አባቶች መካከል ቄስ ሃታና ሃታሳ በበኩላቸው በልዩ ወረዳው በተፈጠረ ግጭት የህብረተሰቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ችግር ገጥሞት ነበር ብለዋል።
"የወረዳው ነዋሪዎች ከመንግስት ጋር በመሆን ለሰላም ባደረጉት ጥረት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ ተደስተዋል" ነው ያሉት።በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ወደነበረበት መመለሱ አርሶ አደሩ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ተማሪው እና የመንግስት ሠራተኛው በነፃነት የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጠቀሱት ቄስ ሃታና፣ የልዩ ወረዳው አመራር አካላት ህዝቡን ያሳተፈ ሥራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኪታንቦ በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ ደራሼ፣ ሞሲዬ፣ ኩስሜና ማሾሌ ብሔረሰቦች እርስ በርስ ተከባብረው በአንድነት መኖራቸውን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በአንድነት ቢኖርም ፀረ-ሰላም ኃይሎች በወረዳው በንጹሀን ላይ በፈጸሙት የጥፋት ተግባር የወረዳው ዋና አመራሮችን ጨምሮ የፀጥታ አካላትም መገደላቸውን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፣ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።
መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃና ህዝበን አሳትፎ በሰራው የጸጥታ ሥራ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ መመለሱን ገልጸዋል።
"የህዝቡ ማህበራዊ መስተጋብር፣ የንግድ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም የመንግስት ተቋማት ወደነበሩበት ተመልሰዋል" ብለዋል።
የአካባቢው ሰላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞ ሰላሙ የተመለሰው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የደቡብ ክልል ልዩ ሃይልና ፖሊስ አባላት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ኃይማኖት አባቶች በጋራ በመሆን ህዝብን በየደረጃው በማወያየት መግባባት ላይ በመደረሱ መሆኑንም አስረድተዋል።
ልዩ ወረዳው ለሁለት ወራት በኮማንድ ፖስት እየተመራ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ የወረዳው ምክር ቤት ሰሞኑን ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ በጎደሉ አመራሮች ምትክ መሾሙን ገልጸዋል።
አቶ ብርሀኑ እንዳሉት የአካባቢውን ሰላም በማወክ በሰብአዊና ቁሳዊ ቀውስ ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ከ800 በላይ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
"ከእነዚህው ውስጥም 350 የሚሆኑት ጉዳያቸው ተጣርቶ የተለቀቁ ሲሆን በቀሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ ነው" ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በወረዳው ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የወረዳው መዋቅር አበክሮ እንደሚሰራ ያስታወቁት አስተዳዳሪው፣ ህዝቡም ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በደራሼ ልዩ ወረዳ ከጥቂት ወራት በፊት በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ የሚታወቅ ነው።