የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል
ሀምሌ 8/2014/ኢዜአ/ የሚጠበቅብንን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ2015 በጀት ዓመት በመዲናዋ 70 ቢሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ማቀዱን ገልጾ ከዚህም ውስጥ ከሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም የእቅዱን 42 በመቶ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን በቅርቡ መግለጹ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የግብር ክፍያን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ግብር ከፋዮች የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ለማረጋገጥ ግብር መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ሲሳይ በላይ፤ ''ግብር ከፋዮች ለምንሰራው ሥራ የሚጠበቅብንን ግብር መክፈል ሀገርን ከመጥቀም ባለፈ እኛም ተጠቃሚ የምንሆንበትን እድል ይከፍትልናል'' ብለዋል፡፡
''ማንኛውም ግብር ከፋይ የሆነ ዜጋ ሀገር አለኝ እስካለ ድረስ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ መወጣት አለበት'' ያሉት ደግሞ ሌላው ግብር ከፋይ አቶ ቃሲም ጣሂር ናቸው፡፡
አቶ ዋሲሁን በቀለም ከግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ግብር ከመክፈል አኳያ የሚኖረው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ ከማኅበረሰቡ የሚሰበሰበው ገቢ ውጤታማ እንዲሆን አሰራሩን ማዘመን ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡