ቀጥታ፡

በአስተሳሰቡና በስራ ባህሉ የላቀ ትውልድ በመገንባት ያልተነካ እምቅ ሀብታችንን ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል-ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

ጅማ፣ሐምሌ 07/2014(ኢዜአ)፡ በአስተሳሰቡና በስራ ባህሉ የላቀ ትውልድ በመገንባት ያልተነካውን እምቅ የሀገር ሀብት መጠቀም እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚል ተናገሩ።

 የኢትዮጵያ ፕሬስ  ድርጅት  ዛሬ በጅማ ከተማ ባዘጋጀው ''ስለ  የኢትዮጵያ''  የፓናል ውይይትና የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ  በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

 ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ እንደ ገለጹት ዜጎች የስራ ባህላቸውን በማሳደግ ኢትዮጵያ የበለጸገች ሀገር እንድትሆን መስራት አለባቸው።

"እኛ ኢትዮጵያውያን ያልተነካ እምቅ ሀብት ያለን መሆኑን ተገንዝበን በአስተሳሰቡና በስራ ባህሉ የላቀ ትውልድ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

ሀገራት የሚከበሩትና ተቀባይነት የሚኖራቸው ባላቸው የኢኮኖሚ አቅም ልክ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ፤"እኛ  መስራት  ያለብን በልተን ለማደር ብቻ መሆን የለበትም" ነው ያሉት።

የቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኮንን እንዳላማው በበኩላቸው የሀገርን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የንግዱን ዘርፍ ማዘመንና ማሳለጥ  ዋነኛው የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

 ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዓለም ሀገራትን በንጽጽር የተመለከቱት አቶ መኮንን፤ ሲንጋፖር ብቻዋን በአለም የንግድ ልውውጥ ስድስት በመቶ ድርሻ  እንዳላት ጠቁመው፤ የአፍሪካ ሀገራት ተደምረው ሁለት በመቶ የማይሞላ ድርሻ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የተሻለ የንግድ ልውውጥና የግብይት ዕድል እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

''ሀገራችን ከውስጥና ከውጭ የገጠሟትን ፈተናዎች አያሸነፈች ዛሬ ላይ የደረሰች በመሆኑ የስራ ባህላችንን አጠናክረን  በኢኮኖሚውም አንቀጥላለን'' ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።

 ከድህነት ለመላቀቅና  ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ለማድረግ  በጋራ በመቆም ለሰላምና እድገት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የ''አሻጋሪ ኮንሰልታንት'' ስራ አስኪያጅና ባለቤት ወይዘሪት መቅደስ ገብረወልድ  በበኩላቸው  የሰው ሃብት እጅግ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት የሰለጠነ አምራች ሃይል  ማፍራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ሽግግርም ሆነ ፈጠራ  ከሰው ብቃት ጋር የሚያያዝ መሆኑን አመልክተው፤ ''ዜጎቻችንን  ማሰልጠን፣ ማንቃትና ክህሎታቸውን ማሳደግ  አማራጭ የሌለው የእድገታችን መሰረት ነው'' ብለዋል።

በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች በተነሳው ሀሳብ ተመስርተው የስራና የምጣኔ ሀብት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥያቄ በመጠየቅና አስተያየት በመስጠት ተሳትፈዋል።

ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች አጋር ተቋማት  ጋር በመተባበር የስራ ፈጠራና ክህሎት ስራዎችን ለመስራት መታቀዱ በመድረኩ  ተገልጿል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋናው አዳራሽ ለአንድ ቀን የተዘጋጀው ''ስለ  የኢትዮጵያ''  የፓናል ውይይትና የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም