ኢንስቲትዩቱ የመንግሥት አመራሮችን ብቃት ለማሻሻል በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የመንግሥት አመራሮችን ብቃት ለማሻሻል በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
ሀምሌ 7/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የመንግሥት አመራሮችን ብቃት ለማሻሻል በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ 7ኛውን ሀገር አቀፍ የአመራርና አስተዳደር የመንግሥት ሴክተር የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሤ ምትኩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና የአመራር ሂደት ጋር የተገናኙ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው።
በዚህም ተቋማት ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲለዩና የማስተካከያ ርምጃ እንዲወስዱ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ ለመንግሥት የፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናታዊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ለብልሹ አስተዳደር በር የከፈቱ አሰራሮችን ለመቀየር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው፤ በጉባኤው የቀረቡ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት አመራሮች በተገቢው ሁኔታ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መስራት ይገባል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማጠናከር በመንግስት አመራሮች በኩል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመድፈን እና የአመራር ብቃትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በምርምር ጉባኤው በመልካም አስተዳደርና በአመራር ይዘት ላይ ያተኩሩ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።