ተቋማት በመልካም አስተዳደር ረገድ ያሉበትን ደረጃ መመዘን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል--የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት በመልካም አስተዳደር ረገድ ያሉበትን ደረጃ መመዘን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል--የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም
ሐምሌ 07/2014 (ኢዜአ)፡ ተቋማት በመልካም አስተዳደር ረገድ ያሉበትን ደረጃ መመዘን የሚያስችል አሰራር ከያዝነው በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተግባራዊ የሚደረገውን አሰራር በሚመለከት ለተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
ሥልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ተቋሙ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስ አይ ዲ/ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ እንደተናገሩት፤ተቋማት መልካም አስተዳደር ተግባራዊ በማድረግ በኩል መሰረታዊ ጉድለቶች እንዳለባቸው ተለይቷል።
"በተለይም ለሕዝብ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ላይ፣ግልጸኝነትና የሕግ የበላይነት መርህን ተከትሎ መሥራት ላይ ክፍተቶች አሉ" ያሉት ዋና እምባ ጠባቂው በዚህ ላይ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ጋር በመሆን ተቋማት በመልካም አስተዳደር ረገድ ያሉበትን ደረጃ መመዘን የሚያስችል መለኪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በመለኪያው መሰረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተቋማት የሚመዘኑ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
መለኪያው አምስት መስፈርቶችን የያዘ ሲሆን እንደ ተቋም ውጤታማ ነው ወይ? ግልጽ የሆነ አሰራር ይከተላል ወይ? በመልካም አስተዳደር ይዞታው ምን ይመስላል? እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ያሰፈነ ነው? የሚለው እንደሚታይም አክለዋል።
ከዚህ ባለፈም አንድ ተቋም አካታች ነው ወይ? የሚለውም በመመዘኛው ይታያል ነው ያሉት።
መመዘኛው የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የተቋቋመበትን አዋጅ መሰረት በማድረግ እንደሆነም አብራርተዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስ አይ ዲ/ ተወካይ አቶ ማንደፍሮህ በላይ በበኩላቸው፤ መመዘኛዎቹ መንግሥት ምን ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበት አቅጣጫ የሚጠቁሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማት የሚመዘኑበት ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተው፤ የተዘጋጁት መለኪያዎች እና መመዘኛዎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቅሰዋል።
መመዘኛዎቹ እንዲዘጋጁ ድርጅቱ አማካሪ ባለሙያዎችን በመመደብ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን የተናገሩት አቶ ማንደፍሮህ ይህም ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር እንዲሻሻል ከፍትሕ ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ገልጸው፤ ከሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ጋርም በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በጋራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።