ቀጥታ፡

በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ ነው

አዲስ አበባ  ሀምሌ 7/2014 /ኢዜአ/ በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም መንግሥት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡   

በዚህም ከታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ የመንና ኦማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ዜጎቹ የሚመለሱት የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለምአቀፉ ፍልሰት ድርጅት /አይ ኦ ኤም/ ጋር በተደረገ የተቀናጀ ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

በሳዑዲ አረቢያ በእሥር ቤቶችና ማቆያ ማዕከላት የነበሩ 102 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውሰው፤ ከእነዚህም ውስጥ ባለፉት ሦስት ወራት ግማሽ ያህሉን ወደ አገር ቤት መመለስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ "ከዒድ እስከ ዒድ" ወደ አገር ቤት ጉዞ መርሃ-ግብርም በርካታ ዜጎች ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጥሪው መሰረት ወደ አገር ቤት የገቡ የዳያስፖራ አባላት የኢትዮጵያ ሙስሊም ታሪክ እና ባህል ኮንፈረንስ ላይ የሚሳተፉና በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ  ተሳታፊ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሳምንታት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ነው ቃል-አቀባዩ የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም