በቻግኒ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት መረጋጋቱ ተገለጸ

126
ባህርዳር መስከረም 3/2011 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ በውሃቢያና በሱፍያ ሙስሊሞች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ማረጋጋት መቻሉን የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ  ለኢዜአ እንደገለጹት ችግሩ የተከሰተው በአዲሱ ዓመት መግቢያ ላይ ሱፍያዎች በሚሰግዱበት ዋናው መስጊድ ውሃቢያዎቹ ገብተን እንሰግዳለን በማለታቸው ነው። በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቀደም ሲል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ሱፍያዎቹ በቻግኒ ዋናው መስጊድ፣ ውሃቢያዎቹ ደግሞ በከተማው ቀበሌ ሶስት ሽሮሜዳ ተብሎ በሚጠራው መስጊድ ለየብቻ ሲሰግዱ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡ ውሃቢያዎቹ በዋናው መስጊድ ወኪል ሊኖረን ይገባል በሚል መነሻም በእለቱ እንሰግዳለን ብለው ሲገቡ በተፈጠረ ግጭትም በ24 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል። ከነዚህም መካከል አራቱ በፀና በመጎዳታቸው ወደ ባህርዳር ፈለገ ህይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተልከው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል። ቀሪዎቹ በአካባቢው በሚገኙ የህክምና ተቋማት ህክምና ተደርጎላቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ኃላፊው ጠቅሰው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጸዋል። ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባትም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የፀጥታ መምሪያ ኃላፊው ሁለቱን ወገን አቀራርበው በማወያየት ችግሩ እንዲረጋጋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም ከክልሉና ከፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በሚመጡ ተወካዮች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል። ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት በከተማዋ ተዘግተው የነበሩ ሱቆችና ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡም የሰላምን ዋጋ ተገንዝቦ ችግሩን ተነጋግሮ በመፍታት ሰላሙን በዘላቂነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባም ኃላፊው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም