ቀጥታ፡

በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ ነው

ሐምሌ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ ወደ አገር ቤት ሊመለሱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በታንዛኒያ ፣ ጅቡቲ ፣ ማላዊ ፣ ኦማን እና ሌሎች አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ 12 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ  መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ዜጎቹን በመመለስ ረገድም የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት /IOM/ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ዜጎቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በሌላ መልኩ በ2ኛው ዙር "ከዒድ እስከ ዒድ" መርሃ ግብር በርካታ ዜጎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ለመርሃ-ግብሩ ወደ አገራቸው የመጡ ዜጎች በአረንጓዴ አሻራ ፣ በተለያዩ ፎረሞች እና በሌሎች መርሃ ግብሮች ላይ እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

ባለፉት ሳምንታት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ውይይት ማድረጋቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም