የኢትዮ-አልጄሪያ የንግድ ትርዒት ለማካሄድ ስምምነት ተደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-አልጄሪያ የንግድ ትርዒት ለማካሄድ ስምምነት ተደረሰ
ሐምሌ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-አልጄሪያ የንግድ ትርዒት ለማካሄድ ስምምነት መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ከአልጄሪያው የንግድና የውጭ ንግድ ፕሮሞሽን ሚኒስትር ካሚል ረዚግ ጋር በሁለቱ ሃገሮች መካከል የንግድ ልውውጥ ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
የሁለቱን ሃገራት መልካም ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የንግድ ግንኙነት ማጠናከር ለመለወጥ ከአልጄሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወደ አልጄሪያ የንግድ ልዑካን ቡድን ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
ለዚህም ተግባራዊነት የኢትጵያን የንግድ ማኅበረሰብ ከአልጄሪያ ገበያ ጋር የሚያስተዋውቅ የመጀመሪያውን የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ለማካሄድ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
በቀጣይ የኢትዮጵያ ምርቶችን በአልጄሪያ ገበያ ለማስተዋወቅ ተመሣሣይ መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ በውይይቱ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ በቅርቡ በአልጄሪያ የነጻነት በዓል በመገኘትና ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብዱልመጂድ ተቡን ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሃገራት መካከል ተጨባጭ የሆነ የንግድ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ በመድረሳቸው ይታወሳል።