ቀጥታ፡

የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሃት ኃይሎች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ አጠናቀቀ

ሐምሌ 06 ቀን 2014(ኢዜአ) የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሃት ኃይሎች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ባለፉት ወራት ባካሄዳቸው ተግባራት ላይ ውይይት አድርጓል።

መንግስት በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ማቋቋሙ ይታወሳል።

የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ካሳ እንዳሉት ግብረ ኃይሉ ዛሬ ባደረገው ሶስተኛው መደበኛ ስብሰባው ያለፉትን ወራት ክንውኖችና ተግዳሮቶችን ገምግሟል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፉና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች ጥምር የምርመራ ቡድን ምክረ ሀሳብ መሰረት በተዘጋጀው የሽግግር ፍትሕ ሪቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቷል።

በዚህም ግብር ኃይሉ በስሩ የተደራጁ አራት ኮሚቴዎች በወንጀል ተጠያቂነት፣ በስደተኞችና ተፈናቃዮች ጉዳይ፣ በሴቶች ጾታዊ ጥቃቶች እና ሀብት ማሰባሰብ ዙሪያ ለሁለት ወራት ያከናወኗቸውን ሥራዎች ገምግሟል ነው ያሉት።

በዚህም የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሃት ኃይሎች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በምርመራ ግኝቱ መሰረት የተፈጸሙ ወንጀሎች አይነቶችና መረጃ ትንተና በመሥራት የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ክስ መመስረት የሚያሰችል ውሳኔ መተላለፉን ነው የገለጹት።

በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ግብረ ኃይሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስራዎቹን ለማከናወን ቢጥርም ከተፈጸሙ ወንጀሎች ስፋትና ውስብስብነት አኳያ በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት ስራውን ለማከናወን ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ገልጸዋል።

ለአብነትም በአፋርና አማራ ክልሎች የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን መረጃ ማጣራት፣ የወደመውን ሀብትና ንብረት መጠን በቤተሰብ ደረጃ መለየት ጦርነቶች ከተደረጉባቸው ስፍራዎች ስፋት አኳያ ትልቅ ፈተና እንደነበርም እንዲሁ።

ለተፈናቃዮችና ጥቃት ለደረሰባቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መንግስት በራሱ አቅም ጥረት ቢያደርግም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተገኘው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑም አንዱ ፈተና ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም