"ሠራዊታችን ሀገር ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የልማት ኃይል መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው" ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
"ሠራዊታችን ሀገር ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የልማት ኃይል መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው" ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ
ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ)"ሠራዊታችን ሀገር ጠባቂ ብቻ ሳይሆን የልማት ኃይል መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው" ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል አራተኛ ዙር ተቋማዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን "ማጽዳት፣ማስዋብ አና ማልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው እለት አስጀምሯል።
በዚህም በዛሬው እለት የተቋሙን ቅጥር ግቢ የማጽዳትና የማስዋብ ስራ የተካሄደ ሲሆን በዋናነት ደግሞ በግብርና ሥራ የስንዴ ዘር የመዝራት ስራ ተከናውኗል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ በተቋሙ የሚገኘውን ሰፊና ለም መሬት ለማልማት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው በዚህም የሠራዊቱን ኑሮ ለመደጎም መታቀዱን ጠቅሰዋል።
"ከሠራን፣ ከለፋን ሀገራችንን መቀየር እንችላላን" ያሉት ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ እንደ ሠራዊት የተሰጠን ተልዕኮ ሀገርን የመጠበቅና መከላከል ቢሆንም የተሰጠንን ጊዜ ተጠቅመን ማልማት ይገባናል ብለዋል።
ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር አስከባሪ ብቻ ሳይሆን የልማት ኃይል መሆኑንም ጭምር ነው የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ የተናገሩት።
የተጀመረው ስንዴ የመዝራት ስራ በቀጣይ ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው የሚተከሉ ችግኞችም ሆነ ሰብሎች ለሠራዊቱ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑን ነው የገለፁት።
የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር መከላከል የሆኑት ብርጋዴር ጀኔራል ኃይሉ መኮንን ፤ ከአሁን ቀደም ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ረገድ ተቋሙ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
አሁን በግቢው ያለውን ሰፊ ቦታ ተጠቅሞ በማረስና ስንዴ በመዝራት ግቢውን ከማስዋብ ባለፈ በሚገኘው ምርት ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
የሠራዊቱን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብና የቢሾፍቱ ከተማን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የአየር ኃይል የውበትና የልማት ቡድን አስተባባሪ ሻለቃ እያሱ ዳጉማ ናቸው።
በዚህም በ30 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጓሮ አትክልቶችን የማልማት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
በልማት ሥራው የተገኙት አርሶ አደር ባልከው መኮንን በበኩላቸው የአካባቢው ማህብረሰብ አየር ኃይልን በእርሻ ሥራ ለማገዝ በዛሬው ዕለት 25 ጥማድ በሬ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ጫካ የነበረ ቦታ ወደ ልማት ተቀይሮ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ ከውጭ ሆኖ ማየት እንኳ የማይቻል የነበረው ተቋም አሁን የህዝብ ተቋም መሆኑን በተግባር አስመስክሯል ብለዋል።