ችግር ብልሃትን ይወልዳል - ኢዜአ አማርኛ
ችግር ብልሃትን ይወልዳል
በዓለም ዙሪያ የተከሰቱ እና እየተከሰቱ ያሉ ድንገተኛ ክስተቶች እና ችግሮች የየሀገራቱን የወጪ እና ገቢ ንግድ ከማስተጓጎል ባለፈ በራሳቸው አምርተው የምግብ ፍጆታቸውን እንዳይችሉ እንቅፋት ሲሆኑ በግልጽ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅ እና አምስት ወራትን ያስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያና ዩክሬን ነዳጅ፣ ስንዴና የግብርና ግብዓት የመሳሰሉትን በማምረት ለዓለም ገበያ በስፋት በማቅረብ ከሚጠቀሱ ቀዳሚ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የሀገራቱ ግጭት ውስጥ መግባት ለዓመታት ከእነዚህ ሀገራት መሰል ምርቶችን ወደ ሀገራቸው ሲያስገቡ የቆዩ በተለይም ታዳጊ ሀገራትን ለከፍተኛ ችግር ዳርጓቸዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ሆነ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የግብርና ምርቶች በሚፈለገው መጠን ወደ ገበያ እንዳይወጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች ዋጋ መናርን አስከትሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገራት የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ወደ ውስጣቸው እንዲመለከቱ፣ ያላቸውንም አቅም እንዲፈትሹ ቢያንስ በምግብ ራስን በሚያስችሉ የግብርና ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል።
ክስተቱ የየሀገራቱን የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ክፉኛ ማስተጓጎሉ እንደተጠበቀ ሆኖ እግረ መንገዱን ሀገራት ችግርን እንዴት ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር እንዳለባቸውም ትምህርት እንደሰጠ መገንዘብ ይቻላል። ለተከሰተው የምግብ አቅርቦት ችግር መፍትሔ ለመሻት ሲሉም የውስጥ የምግብ ፍጆታቸውን በራሳቸው አቅም እንዴት ማምረት እና መሸፈን እንደሚችሉ ጭምር አዳዲስ ስልቶችን እንዲነድፉ አስገድዷል። ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ችግሮችና ክስተቶች ትምህርት ከወሰዱ እና የራሳቸውን የምግብ ፍጆታ መሸፈን የሚችሉበትን አማራጭ ስልት ተግባራዊ ካደረጉና እያደረጉ ካሉ ሀገራት መካከልም አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡
እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ወቅቶችን እንዴት መሻገር እንዳለባት ወትሮም ብልሃት የማታጣው ኢትዮጵያ አሁንም በዚህ ዘመን በርካቶችን ለከፋ ጉዳት የዳረጉ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚነት በመቀየር ውጤት በማስመዝገብ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ ችግር ብልሃትን ይወልዳል የሚለውን ሀገራዊ ብሂል በመርህነት በመያዝ ከውጭ ከሚመጣ የግብርና ምርት ጥገኝነት ለመላቀቅ የጀመረችው የበጋ መስኖ የግብርና እንቅስቃሴ ስንዴን በስፋት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት አልፋ፤ የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግብ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህ ግብ እውን ሊሆን እንደሚችልም በበጋ መስኖ የተገኘው የስንዴ ምርት ማሳያ ይሆናል፡፡ ለዚህም በጥቂት የመንግስት ድጋፍ በመበረታታት በዘርፉ ተሰማርተው ቀደም ሲል በበጋ ወቅት ሲያገኙ ከነበረው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የግብርና ምርት በመውጣት አሁን ላይ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ በማድረጋቸው ያገኙትን ጥቅም የሚመሰክሩ አርሶ አደሮች እየተበራከቱ መምጣት በዋቢነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው።
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የስንዴ ምርቷን ለናይጄሪያ ልታቀርብ ነው፡፡ ናይጄሪያም የህዝቧን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ስንዴ ከኢትዮጵያ ልታስገባ ነው የሚሉ ዘገባዎች በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ዘገባዎች ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልም ሆነ የግብርና ምርቶቿን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የያዘችውን ዕቅድ እንደምታሳካ ተስፋ ሰጪ የሆኑት ስራዎች መተማመኛ ናቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ ቀደም ሲል የክረምት ዝናብን ብቻ ጠብቆ ያካሒድ የነበረውን የምርት እንቅስቃሴ በበጋ መስኖ አማካኝነት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴና በግብርና ሜካናይዜሽን በመታገዝ መስራቱ ምርታማነትን እንዲያሳድግ አስችሎታል፡፡ ለዚህም ቀደም ሲል በበጋ ወቅት የእርሻ መሬታቸውን ተጠቅመው ከተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ሲያገኙ የነበሩትን አነስተኛ ጥቅም አሁን በአዲሱ የግብርና ቴክኖሎጂ አማካኝነት ካገኙት ጋር በማነጻጸር የልዩነቱን ስፋት ኢዜአን ጨምሮ ለሀገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን የተናገሩትን አርሶ አደሮች ተሞክሮ ማየቱ በቂ ነው።
ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በበጋ መስኖ ግብርና ላይ ብቻ ማተኮር ብቸኛ መፍትሔ እንደማይሆን ይልቁንም በተገኙ አጋጣሚዎችና ምቹ ሁኔታዎች ሁሉ የግብርና ምርትን በማሳደግ በምግብ እጥረት ከሚከሰት ድርቅ ብቻ ሳይሆን ይህን እንደምክንያት በመጠቀም በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ከሚዳዳቸው የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ራስን ነጻ የማውጫ መንገድም ጭምር እንደሆነ ታምናለች፡፡ በዚህም በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረጉ የበጋ መስኖ ጥረቶች በተጨማሪ ምግባችንን ከጓሯችን በሚል መሪ ቃል መላ ህዝቡ በመኖሪያ እና በሚሰራባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚገኙ ስፍራዎችን በጓሮ አትክልት እንዲሸፍን በመደረጉ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘበት እንደሆነም ማየት ተችሏል።
ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንደሚባለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የግብርና ምርቶች መወደድ የኢትዮጵያ መንግስትንና አርሶ አደሮችን ብሎም መላ ህብረተሰቡን አነቃቅቶ ምርት እና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ጥሩ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ለዚህም ነው በመላ ሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው ምግባችንን ከጓሯችን ንቅናቄ ፍሬ እያሳየ ያለው፡፡ ቀደም ሲል በበጋ ወቅት የተወሰነውን ማሳቸውን ብቻ በጓሮ አትክልት ሲሸፍኑ የነበሩ አሁን ወቅታዊውን ሁኔታ ለመጋፈጥ በመወሰን የስንዴ ምርት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደሮች የእስከ ዛሬው መሳሳታችን ይበቃናል ከዚህ በኋላ በምንም ምክንያት ወደ ኋላ አንመለስም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ምንም እንኳን በቂ እንዳልሆነ ቢታወቅም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፌዴራሉ መንግስት እና የክልል መንግስታት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን በማመን ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የግብርና ግብዓቶችን ጨምሮ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የተለያዩ ማሽነሪዎችን (ትራክተሮች እና ኮምባይነሮችን) ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ ይህም በሁሉም አካባቢ ይበልጥ ቢሰፋ የዘርፉ ትንሳኤ ሩቅ እንደማይሆን ግልጽ ነው። ይህንን የተረዱ አርሶ አደሮች የበለጠ ተጠቃሚ ያሚያደርጋቸውን የግብርና ግብዓት መንግስት እንዲያቀርብላቸው እየጎተጎቱ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ እጥረት ችግር ተከሰተ ሲባል እጅግ የሚገርማቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቱ በግብርና ምርት በኩል ከራሷ አልፋ ለሌሎች መደጎም የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት በተለያዩ ጥናቶች በማረጋገጣቸው ነው፡፡ በክረምት ወቅት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወቅትም ጭምር ቢዘራበት ማብቀል የሚችል ለም መሬት፣ ውሃ እና አምራች ሀይል በስፋት እንዳላት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በምርታማነታቸው ከሚጠቀሱት የሀገሪቱ አካባቢዎች በተጨማሪ እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቢሰራባቸው የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላቸው በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
ይህ እምቅ አቅም በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እንዳለ የተረዳው መንግስት በዘርፉ የተሻለ ምርት ማግኘት የቻሉ አካባቢዎችና አርሶ አደሮች ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እና የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ተሞክሮዎች እንዲሰፉ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ወደ ግብርናው እንዲገቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍም ይበል ያሰኛል።
የሚያጠግብ እንጀራ … እንዲ መሰል የግብርና ግብዓቶችንና ሙያዊ ድጋፎችን በተለይም በአቅማቸው ልክ በስፋት ባልተሰራባቸው አካባቢዎች በማቅረብ የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር ከሁሉም ይጠበቃል። የመንግስትና የፖለቲካ አመራሮች የግብርና ባለሙያዎችን፣ አርሶና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ለላቀ ውጤት መትጋት በድህነት ከመጉበጥ የሚያድን ቁልፍ አማራጭ እንደመሆኑ ርብርቡ መቀጠል አለበት። በዚህ ታሪካዊ የትውልድ ሃላፊነት ላይም በግብርናው ዘርፍ በላቀ ሁኔታ ከምሁራን ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ይገባል።