የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማምረቻው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማምረቻው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጀ
ሀምሌ 6/2014/ኢዜአ/ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
አቶ መላኩ ይህን ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአምራች ኢንዱስትሪው ማህበራት ጋር በዘርፉ ያለውን ተግዳሮት ለመፍታት ያለመ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ባካሄዱበት ወቅት ነው።
በውይይቱ የተሳተፉ አምራች ማህበራት በዘርፉ የሚጠበቀውን እንቅስቃሴ ለማድረግ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ጠቅሰው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።
የጥሬ ዕቃ ግብዓት፣ የውጭ ምንዛሬ፣ ብቁ የሆነ የሰው ሃይል እጥረት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመሰረተ ልማት አለመሟላት የማምረቻ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳይራመድ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ችግሮቹ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ከማድረግ አልፈው ሀገሪቱ የተሻለ ገቢ እንዳታገኝ እያደረጓት ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው በዘርፉ የሚነሱ አብዛኞቹ ችግሮች ከፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ችግሮችን የሚፈታ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የገለጹት።
የማምረቻ ኢንዲስትሪው በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ሆኖም፤ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ያሉ ችግሮች እየተቃለሉ ቢመጡም አሁንም የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም እንዲሁ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ የአስር ዓመት ዕቅድ ላይም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ቅድሚያ ሰጥቶ ለመፍታትና የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብ ትኩረት ተደርጓል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የህግ ማሻሻያዎችን ከማድረግ በተጨማሪ ከባለሀብቶች ጋርም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታትና ተወዳዳሪ ለማድረግ፤ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎም ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያነሱትን የብድርና የውጭ ምንዛሬ ችግሮች ለመፍታትም ከባንኮች እና ከተለያዩ አካላት ጋር በመስራት ጥሩ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።