የደቡብ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት መደራጀቱ የዘርፉን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት መደራጀቱ የዘርፉን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ተገለጸ
ሀዋሳ3/1/2011 የደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት መደራጀት በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል ተገለጸ፡፡ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሃምሌ 1/2010 ዓ.ም. አንስቶ ያልተማከለ አስተዳደር መከተል ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ጂኦግራፊያዊ /መልካምድራዊ / አወቃቀር እንደነበረው አመልክተው "አዲሱ አደረጃጀት የፌዴራል ስርዓቱን ተከትሎ በክልል ደረጃ የተዋቀረ ነው "ብለዋል፡፡ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም በአዲሱ አደረጃጃት አምስት ዲስትሪክቶች በሀዋሳ፣አርባምንጭ፣ወላይታ ሶዶ፣ቦንጋና ሆሳዕና እንዳሉት አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ደንበኞች ከዚህ ቀደም በሚጠቀሙት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያልተፈፀሙ ጉዳዮቻቸው በአቅራቢቸው ባሉ አዳዲስ ዲስትሪክቶች ምላሽ እንደሚያገኙም ጠቁመዋል፡፡ ስራ አስፈጻሚው እንደገለጹት የአደረጃጀት ለውጡ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡ አዲሱን አደረጃጀት በመጠቀም የኤሌክትሪክ መሰረት ልማት ተደራሽነቱን ማስፋት የበጀት አመቱ ትኩረት እንደሆነ ጠቁመው " የ76 ቀበሌዎችን ኤልክትሪክ አገልግሎት የማገናኘት ስራ ይከናወናል" ብለዋል፡፡ ከ4ሺህ 500 በላይ ከፍተኛና ዝቅተኛ መስመሮችን በአዲስ መስመር ማገናኘትና ከ1ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮችን የመትከል እቅድ መያዙንም ስራ አስፈጸሚው አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ከ162ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን በአዲስ መልኩ በኤሌክትሪክ ቆጣሪ የማገናኘት ስራ እና ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ከ1ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ እንደሚከናውንም ተናግረዋል፡፡ ተግባራቱ አገልግሎቱ ከሚሰበስባቸው ገቢዎች የሚፈጸሙ በመሆናቸው በዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ለዚህም ህብረተሰቡ በወቅቱ የአገልግሎት ክፍያውን ሊፈጽም እንደሚገባ ስራ አስፈጸሚው አሳስበዋል፡፡ "በሃገሪቱ ስምንት ከተሞች የተጀመረው ኔትወርክ በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በሃዋሳ የሙከራ ትግበራ ላይ ነው "ያሉት አቶ ክንፈ በአንድ ጊዜ የሚጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ እንደቀነሰም ጠቁመዋል፡፡ ለኃይል መቆራረጥ ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፣ለአገልግሎት ክፍያ የሚመጡ ደንበኞችን በተገቢው አለማስተናገድንና ሌሎችም የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዓመቱ ትኩረት ይደረግባቸዋል፡፡ "በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮች ተለይተዋል "ያሉት ስራ አስፈጸሚው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ዛፎችን በዘመቻ የመቁረጥና ደረጃቸውን ሳይጠብቁ የተዘረጉ የኤሌትሪክ መስሮችን የማስተከካል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ " ያረጁ ኔትወርክ መስመሮችና ፖሎች/ምሶሶዎች/ መቀየርና ከልክ በላይ የጫኑ ትራንስፎርመሮችን አቅም ማሳደግ በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮች ናቸው" ብለዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እንሚፈቱ ጠቁመው ህዝቡ መሰረተ ልማቶችን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡