ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ22 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ በአስፋልት ደረጃ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ22 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ በአስፋልት ደረጃ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘርፍ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት አገልግሎት ዙሪያ ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መድረክ አካሂዷል።  

በምክር ቤቱ ቀርበው ገለጻ ከሰጡ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመንገዶች ግንባታ በፍጥነት አለመጠናቀቅ፣ የጥራት ችግሮችና ተደራሽነት ላይ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።        

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 160 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ጠቅሰዋል።     

ለመንገዶቹ ግንባታ እስካሁን 414 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቁመው የመንገድ ሽፋኑ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።     

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የመንገድ ሽፋኑን ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን አስታውሰው ለዚህም የሚረዱ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።     

በአሁኑ ወቅት ከ22 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ በግንባታ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።  

የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚጠበቀው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ የጸጥታና የተቋራጮች አቅም ማነስ መንስኤዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።    

የፕሮጀክት ጊዜና ፋይናንስ አቅርቦት አለመጠናቀቅ፣ በክልል እና ፌደራል መንግስት የሚገነቡ መንገዶችን ያለመለየት ችግሮችንም በምክንያትነት አንስተዋል።   

አስተዳደሩ ለካሳ ክፍያ ብቻ 10 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የተናገሩት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ የካሳ ክፍያ አሰራሩም በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

አስተዳደሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ፖሊሲና አዋጅ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።        

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተቋማቸውን እንቅሰቃሴ አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ፤ በአገሪቱ የቴሌኮም ተደራሽነትን ለማስፋት አዳዲስ አሰራሮችን እያስተዋወቅን ነው ብለዋል።  

ዓለም አሁን የደረሰበትን የአምስተኛው ትውልድ /5ጂ/ አገልግሎትንም በሙከራ ደረጃ መተግበር መጀመሩን በማንሳት።    

ኩባንያው ባለፉት ሦስት ዓመታት የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ ማድረጉን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል።   

በቴሌኮም አገልግሎት ላይ መቆራረጥ እየተከሰተ ያለው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ነው ብለዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ስርቆት፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና የጸጥታ ችግሮች ለአገልግሎቶች መቋረጥ አስተዋጽኦ አላቸው።     

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከህዝቡ በሚነሱባቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ያላቸውን ምላሽ አዳምጧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም