በአፍሪካ የሰላም ግንባታ ሒደት ውስጥ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

16

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ የሰላም ግንባታ ሒደት ውሰጥ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ የ2022 የወጣቶች የምክክር መድረክ "ወጣቶች ለሰላም ግንባታና አካባቢ ጥበቃ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

መድረኩ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በመከላከያ ሚኒስቴር እና በምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አማካይነት የተዘጋጀ ሲሆን ለሁለት ቀናት ይቆያል።

በመድረኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 በላይ አገራትን የሚወክሉ ወጣቶች  ተገኝተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመድረኩ እንደናገሩት፤ በአፍሪካ 75 በመቶው የሚሆነው ህዝብ ከ35 ዓመት በታች ያለ ወጣት በመሆኑ ይሕንን  አቅም መጠቀም ተገቢ ነው።

"ወጣቱን ያላሳተፈ የሰላም ግንባታ ስራ የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብበት አይችልም " ነው ያሉት፡፡

በተናጥል የሚደረግ የሰላም እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት ማረጋገጥ ስለማይችል እንደ አህጉር በጋራ ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያም የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መስራች አገር እንደመሆኗ የአህጉሪቱን ሕዝቦች በማስተባበር ረገድ የሚጠበቅባትን ለመወጣት እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ወጣቶችን በሰላም ግንባታ ስራ በማሳተፍ የአፍሪካን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥን አላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የሰላም ግንባታ ስራው አካል እና የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አስረድተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ከ 1951 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ህብረት ስር በተለያዩ አገራት ሰላም በማስከበር ጉልህ ሚና መጫወቷን አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም  በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከበር ውስጥ በተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰላም የልማት ቅድመ ሁኔታ  በመሆኑ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ ወጣቱ የበኩሉን እንዲያበረክት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

"ጥይት የማይጮህባት አፍሪካን" እውን ለማድረግ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዳይሬከተር ብርጋዴር ጀኔራል ቃቢሳ ዶሚቲያን ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ "ቀጠናውን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት የአፍሪካ ወጣቶች ለሰላም ጥብቅና መቆም አለባቸው" ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከሰላም ግንባታ በተጨማሪ በአረንጓዴ ልማት ዙሪያም ምክክር እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም