ወጣቶች ከጥፋት ቡድኖች ሴራ ራሳቸውን ጠብቀው በሰላም እሴት ግንባታው ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል

21

ጂንካ ፤ሐምሌ 5/2014(ኢዜአ)ወጣቶች አፍራሽ አስተሳሰቦችን እና እኩይ ድርጊቶችን አንግበው ከሚሰሩ የጥፋት ቡድኖች ሴራ ራሳቸውን ጠብቀው በሰላም እሴት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ አስገነዘቡ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ከ 120 ሺህ በላይ ወጣቶችን ያሳተፈ የክረምት ወራት የወጣቶች  የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ደም በመለገስ፣ ችግኝ በመትከል ና የአቅመ  ደካሞችን  ቤት  በማደስ  ተጀምሯል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ  በዚሁ ጊዜ  እንዳሉት  ወጣቶች  አፍራሽ  አስተሳሰቦችን  እና እኩይ ድርጊቶችን አንግበው ከሚሰሩ የጥፋት ቡድኖች ሴራ ራሳቸውን ጠበቀው በሰላም እሴት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ  ሊያደርጉ ይገባል።

የዞኑ ወጣቶች ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ  ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን መስጠታቸውን አስታውሰው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

በዞኑ ዛሬ በተጀመረው የክረምት  ወራት የበጎ  ፈቃድ አልግሎት  ስራዎች   ወጣቶች  ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም አቶ ንጋቱ አሳስበዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ወጣቶች  ህብረተሰቡን  የሚያገለግሉበት  ብቻ ሳይሆን  ከአከባቢው  ህብረተሰብ  ጠቃሚ ልምዶችን፣ የአብሮነት እሴቶችን፣ ባህሎችንና  ትውፊቶችን የሚቀስሙበት መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና  ስፖርት  መምሪያ  ኃላፊ አቶ  ዳግም መኮንን ገልጸዋል።

በክረምቱ ወራት የበጎ አገልግሎቱ ወጣቶች ባላቸው ዕውቀት፣ልምድና ዝንባሌ በ13 የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እስከ 96 ሚሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

ወጣቶቹ በትምህርት ዘርፍ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት፣ አጫጭር  የኮምፒውተርና የቋንቋ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የትምህርት ቤቶችን ግቢ ማፅዳትና ክፍሎቹን ለ2015 የትምህርት ዘመን ምቹ የማድረግ ስራዎችን ያከናውናሉ ብለዋል።

በጤናው መስክ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ የግንዛቤ የመፍጠር፣ ለወባ ትንኝ  መራቢያ የሆኑ  አካባቢዎችን  የማፅዳት፣ የደም ልገሳና ሌሎች አግልግሎቶችን እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

እንዲሁም ድጋፍና እንክብካቤ ለሚሹ ወገኖች  ተቋማትን  በማስተባበር  ድጋፍ የማድርጉ  ሲሆን፤  የ273  አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን  የማደስ፣  የመጠገንና  የመስራትና   ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት  የማሰባሰብ  ተግባራትን  ያከናወናሉ  ብለዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ወጣቶቹ በአረንጓዴ አሻራ የማኖር መረሃ ግብር ከ14 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞችን እንደሚተክሉም አስታውቀዋል።

በዞኑ በአምናው የክረምት በዘንድሮው የበጋ ወራት ወጣቶች በሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ 490 ሺህ የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ  ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከወጣቶቹ መካከል የሰሜን አሪ ወረዳ የገሊላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይስሃቅ ቀፃዮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ ማህበረሰቡን ከማገልገል ባለፈ የሚሰጠን የህሊና እርካታ ላቅ ያለ ነው ብሏል።

ወጣት አብዮት ጌታቸው በበኩሉ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መለገሱን ችግኝ በመትከልም በአረንጓዴ ልማት አሻራውን ማኖሩን ገለጾ፤ በአገልግሎቱ በንቃት በመሳተፍ ማህበረሰቡን ለመጥቀም እንደሚሰራም አስረድቷል።

በጂንካ ከተማ የመኖሪያ ቤት እድሳት  የተጀመረላቸው   ወይዘሮ አልማዝ  ተረፈ  አቅመ ደካማ  በመሆናቸው  ደሳሳ  ጎጇቸውን  ማደስ  አለመቻላቸውን  ገልፀው ክረምት በገባ ቁጥር ቤቱ ስለሚያፈስ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።

የዞኑ አመራሮች፣የመንግስት ሰራተኞችና በጎ ፈቃድ ወጣቶች ችግራቸውን ተመልክተው ደሳሳ ጎጇቸውን ለማደስ በመወሰናቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም