ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ለህዝቦች ተጠቃሚነት ተስፋ የሰጠ መሆኑ ተገለጸ

አክሱም መስከረም 3/2011 የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት ግንኙነት መጀመር ድንበር አካባቢ ላሉ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች  በልማት ተጠቃሚ ለመሆን  ተስፋ ሰጪ መሆኑን በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ፡፡ ለኤርትራ ድንበር ቅርብ ከሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ራማ አንዱ  ነው፡፡ የራማ ከተማ ነዋሪ አቶ መብራህቱ ንጉሰ ለኢዜአ እንዳሉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አብይ አህመድ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ጋር ያደረጉት ሰላማዊ ግንኙነት ከኤርትራዊያን ወንድምና እህቶች ጋር አብሮ ለመኖር ተስፋቸውን ያለመለመ  ነው፡፡ የግንኙነቱ መጀመር  ለሁለቱ ሀገራት  ዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አቶ መብራህቱ  እንዳሉት ላለፉት ሀያ ዓመታት ድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦች  በሁሉም መስክ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ተቋርጦ የነበረው የድንበር አካባቢ ንግድ በፍጥነት እንዲጀመር ፍላጎታቸው እንደሆነ  ነው የገለጹት፡፡ በቅርቡም  ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኤርትራ በመሸጋገር  ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው በመመለሳቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ ጽጌ ገብረእግዚአብሔር  የተባሉ ከተማው  ነዋሪ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት  ህዝቦች መቀራረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት የሁለቱ ሀገራት ነጋዴዎች በራማ ከተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ይመላለሱ እንደነበር አውስተው አሁንም ግንኝነቱ  ወደ ነበረበት ይመለሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ " ሁለቱ ወንድምና እህት  ህዝቦች  ለአንድ ቀን መለያየት አልነበረባቸውም"  ያሉት ደግሞ አቶ ካልአዩ ሃፍተ  የተባሉ ሌላው የራማ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ከ20 ዓመታት በፊት ወጣት በነበሩበት ወቅት ወደ አስመራና ዓዲ ኳላ እየተመላለሱ ይነግዱ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ " አሁንም  ሰላሙ ወደ ነበረበት እንዲመለስ የበኩሌን እወጣለሁ " ብለዋል ። በሁለቱም   ሀገራት መካከል ሰላም መፈጠሩ  በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችም መልሶ ለማልማት እንደሚያግዝ አቶ  ካልአዩ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ዓመት ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የሰላም፣የልማት እና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም