ቀጥታ፡

ሕብረቱ ለአቅመ ደካሞች ቤት መስሪያ የሚሆን የቤት ክዳን ቆርቆሮ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ደሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የወሎ ነጋዴዎች ሕብረት በደሴ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ቤት መስሪያ የሚሆን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

ከሕብረቱ ተወካዮች መካከል አቶ ሰይድ አህመድ እንዳሉት ወቅቱ እርስ በርስ መደጋገፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ሀላፊነት አለበት፡፡

ሕብረቱ በወሎ አካባቢ የሚደረገውን መልሶ የማቋቋም ሥራ ከመደገፍ ባለፈ መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚኖሩ ዜጎች ቤት ለመስራት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

በድጋፉ ከ1 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ 1 ሺህ 275 የቤት ክዳን ቆርቆሮ እና 25 ባኮ ሚስማር ለደሴ ከተማ አስተዳደር ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ሰይድ የገለጹት።

ድጋፉን የተረከቡት የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሱሌማን እሸቱ በበኩላቸው መንግስት የመኖሪያ ቤት ለሌላቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች በሚችለው አቅም ቤት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በደሴ ከተማ በሚገኙ 5 ክፍለ ከተሞች በህዝብ ለተለዩ 54 አቅመ ደካሞችም አዲስ ቤት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "ዛሬ የተደረገልን ድጋፍ ተጨማሪ ቤቶችን ለስራት እድል ይሰጠናል" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹን እየሰራ ያለው በራሱ ከመደበው በጀት በተጨማሪ ህብረተሰቡንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ጭምር መሆኑን ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም