ቀጥታ፡

አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ አደነቀች

አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ መሞገስ እንደሚገባው የአሜሪካ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአፍሪካ የዓለም አቀፍ ጤና፣ ሰብዓዊ መብቶችና ተቋማት ንዑስ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ክሪስ ስሚዝ ተናገሩ። ሚስተር ክሪስ ስሚዝ ከሶስት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆኑ፤ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል። ''በቆይታዬ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አይቸው የማላውቀው ከፍተኛ የለውጥ ስሜትና ጉጉት ተመልክቻለሁ'' ሲሉ ነው በኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ መብት አከባበር በሚከታተለው ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ። ''ባለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያን ከሰብዓዊ መብት ጋር በማያያዝ ስንወቅሳትና ስንተቻት ቆይተናል'' ያሉት ክሪስ ስሚዝ፤ ''ዛሬ ወቀሳን ሳይሆን ሙገሳን እናቀርብላታለን'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት አንስቶ "ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን የለውጥ ጉዞ እናደንቃለንም" ብለዋል። ከአንድ ዓመት በፊት በአገሪቷ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች መፍታት፣ ከኤርትራ ጋር ገጥማው የነበረው አለመግባባት ለአገሪቷ ፈተና እንደነበሩ ነው የገለጹት። ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ ፖለቲካ እንዲሳተፉና ሲቪል ማህበራት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ኤች አር 128 በሚለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሳሰቢያ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል። ይህን ተከትሎም በውጭ አገር የነበሩና በአገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብት አያያዝ በአገሪቷ እንዲከበር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ "ለውጥ እየተመዘገበ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እያደረጉት ያለው ለውጥ አሜሪካ በኤች አር ያቀረበችውን ጥያቄ ያካተተ በመሆኑ እንደ ጥሩ ጅምር ይታያል ነው ያሉት። ከታዩ ውጤቶች መካከልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንዲፈቱ ማድረግ ሁለቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶሶች ማስማማት፣በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ የተባለ የሰላም ስምምነት ማድረግን ለአብነት ጠቅሰዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ "የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የለውጥ ስራ የሚደነቅ ነው" ያሉት ኃላፊው፤ የተጀመረው ስራ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ አጋጣሚ በመሆኑ ትውልዱ አጋጣሚውን ሊያባክነው አይገባም ሲሉ መክረዋል። ወደ ፊትም የጸረ ሽብር ህጉ ማሻሻል እንደሚገባ፣ በአገሪቷ ከመኖሪያ መንደራቸው የተፈናቀሉ ግለሰቦች በአፋጣኝ ወደ ነበሩበት ቦታ መመለስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ኢኮኖሚውን ክፍት ለማድረግ በከፊል ለባለሃብቶች ለመተላለፍ የተዘጋጁት ግዙፍ ተቋማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። አሜሪካም የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ ከፍተኛ እገዛ እንደምታደርግና ጠንካራ አጋርም ሆና እንደምትቀጥልም ገልጸዋል። የኮሚቴው አባል የሆኑት የሪፖብሊካን ፓርቲ አባል ወይዘሮ ካረን ባስ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ በኢኮኖሚ አቅሟ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለችው "ኢትዮጵያ ቀጣናውን በተመለከተ የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ናት" ብለዋል። ኢትዮጵያ ካለመረጋጋት በመውጣት በአፍሪካ ወጣት ለሆነው መሪዋ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አከናውናለች በማለት ካረን ባስ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩት ለውጦች  የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እየሳቡ ቢሆኑም "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ፈታኝ የሆኑ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው እናውቃለን" ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል። ''ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ በምን መልኩ መጓዝ አለበት የሚለውን ተገንዝበን ድጋፋችንን ልንሰጥ ይገባናል'' ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም