ኦሮሚያ ባንክ የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች 2022 የአገልግሎት ጥራት ተሸላሚ መሆኑን ገለጸ

146

ሐምሌ 6/2014(ኢዜአ) ኦሮሚያ ባንክ የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች 2022 የአገልግሎት ጥራት ተሸላሚ መሆኑን ገልጿል።

ሽልማቱ ባንኩ በዓለም-አቀፍ ንግድ እና ባለፉት ሁለት ዓመታት ባደረገው ሁሉ አቀፍ አገልግሎት የተገኘ መሆኑም ተገልጿል።

የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን ሽልማቱን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባንኩ የአገልግሎቱ ጥራት ተሸላሚ መሆኑ በአገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ፋና ወጊና ተምሳሌት ከመሆን ባለፈ ለአገርም ኩራት መሆኑን አስመስክሯል ነው ያሉት።

የጥራት ሽልማቱ በስፔን ባርሴሎና የተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ35 አገራት የተወጣጡ የተለያዩ ድርጅቶች ተወዳድረው የኦሮሚያ ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች 43 ኩባንያዎች ተሸላሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባንኩ ይህን ሽልማት ሊያገኝ የቻለው አመራሩና ሰራተኛው በጥንካሬና በቅንጅት ተባብረው በመሥራታቸው ነው ብለዋል።

ሽልማቱ ባንኩ በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንዲሠራ ተነሳሽነት እንደፈጠረለት ጠቁመዋል።

በሽልማት መርሃ ግብሩ ከአምስት የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ አምስት ኩባንያዎች ብቻ የጥራት ሽልማቱን መውሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኦሮሚያ ባንክ ተሸላሚ ሆኗል።

ኦሮሚያ ባንክ በዚህ ዓመት ያልተጣራ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱ ተጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች የጥራት ሽልማት መውሰዱ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም