የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ዙሪያ ውይይት ሊያደርግ ነው

94

ሐምሌ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ዙሪያ የፊታችን ሰኞ ውይይት እንደሚያደርግ ተገለጸ።

ኮሚቴው ውይይቱን የሚያደርገው ኢትዮጵያ አበዳሪዎች የብድር ማስተካከያ የሚያደርጉበትን የጊዜ ገደብ በግልጽ እንዲያስቀምጡ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።

የእዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ መወሰድ ባለባቸው የፋይናንስ እርምጃዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ዘጠነኛው የፓሪስ ፎረም ከሰሞኑ መካሄዱ ይታወቃል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ አበዳሪዎች የቡድን 20 የብድር ማገገሚያ የጋራ ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ የእዳ እፎይታውን መቼ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በግልጽ ማሳወቅና ማዕቀፉን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው ነበር።

የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በብድር ክፍያ ሽግሽግ ላይ ሰኞ እንደሚወያይ ያሳየው የሮይተርስ ዘገባ ውይይቱ ከሚካሄድበት ቀን ውጪ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ አላወጣም።

ኢትዮጵያ በፓሪሱ ፎረም ላይ በጋራ ማዕቀፉ የምታገኘው የብድር እፎይታ(ማገገሚያ) መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገሪቷን የእዳ ጫና ለመቀነስ ተግባራዊ እያደረገ ካለው ስትራቴጂ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን ጠይቃለች።

ሚኒስትር ዴኤታው ከዘጠነኛው የፓሪስ ፎረም ስብስባ ጎን ለጎን ከተለያዩ ባለስልጣናት ባለሀብቶች ጋር መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዶክተር እዮብ ከፓሪስ ክለብ የጋራ ሊቀመንበር ዊሊያም ሮስ፣ከአሜሪካ ግምጃ ቤት ምክትል ረዳት ጸሐፊና የፓሪስ ክለብ የአሜሪካ ልዑክ ፓትሪሺያ ፖላርድ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ያቀረበችውን የዩሮ ቦንድ ከገዙ ባለሀብቶች በብድርና የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።

የቡድኑ አባል አገራት እና የፓሪስ አበዳሪዎች ክለብ እ.አ.አ 2020 ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት እ.አ.አ መስከረም ወር 2021 የኢትዮጵያን የእዳ እፎይታ ጥያቄ የሚመለከት ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል።

ፈረንሳይ እና ቻይና የአበዳሪዎቹን ኮሚቴ በሊቀመንበርነት የሚመሩ አገራት ናቸው።

ኮሚቴው እ.አ.አ በመስከረም ወር 2022 በብድር ማስተካከያ ላይ ውይይት አድርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ተጨባጭ ውሳኔዎችን ሳያሳልፍ ቀርቷል።

የአበዳሪ አገራት የጋራ ማዕቀፍ የቡድን 20 አገራትን እና የፓሪስ ክለብ የሚባሉትን አበዳሪዎች በማስተባበር የታዳጊ አገሮችን ዕዳ እንደ የአገሩ ሁኔታ ለማጤን የሚያስችል ስርዓት ይከተላል።

የፓሪስ ክለብ አሜሪካ፣እንግሊዝ፣ፈረንሳይን ጨምሮ የ22 አገራት አበዳሪ ተቋማትን ያካተተ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም