የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት ተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት ተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
ሐምሌ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ ጉዳይ ላይ የተማሪውን አካል ጉዳተኝነትና ህሙማንን ታሳቢ በማድረግ ውሳኔ አሳለፈ።
በፋርማሲ፣ በህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ፣ በህክምና ራዲዮሎጂ እንደ ምርጫው ትምህርቱን እንዲቀጥል ምክረ ሀሳበ መቅረቡንና ተማሪው በመረጠው ዘርፍ እገዛ ይደረግለታል ተብሏል።
በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ5ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ የሆነው ቢኒያም ኢሳያስ ቅሬታ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።ተማሪው በተፈጥሮ ምክንያት የአንድ እጅ አካል ጉዳት ያለበት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርትን መቀጠል አትችልም ብሎ ትምህርቱን እንዲያቋርጥና ሌላ ትምህርት እንድጀምር ውሳኔ አሳልፏል ሲል ቅሬታ አሰምቶ ነበር።
በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሰዎችን ሲያነጋግር በነበረው ጉዳይ ላይ ዩኒቨርሲቲው መግለጫ ሰጥቷል።
በማብራሪያው በተማሪ ቢኒያም ጉዳይ በአንድ በኩል የተማሪው መብት እንደ አካል ጉዳተኛና ተማሪ በሌላ በኩል ደግሞ የህሙማን ደህንነትና ህይወትን አስቀምጦ በርካታ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ፤ ተማሪው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርቱን ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።
ተማሪው የ4ኛ አመት የህክምና ትምህርቱን በመከታተል ላይ እያለ በተፈጥሮ በግራ እጁ ላይ የአካል ጉዳት እንዳለበት በመምህራኑ ታይቶ ጉዳቱ የህክምና ትምህርቱን መቀጠል ከማስቻል አንጻር በትምህርት ቤቱ ዲን እንዲታይና እንዲወሰን ለዲን ጽህፈት ቤት መቅረቡን ተናግረዋል።
ይህ ጥያቄ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ስምንት ወራት የተማሪው ጉዳይ ትምህርት ቤቱ ኮሌጁ እና ዩኒቨርሲቲው ሲከታተሉት መቆየታቸውነ አንስተዋል።በዚህም ዩኒቨርሲቲው፣ ኮሌጁና ትምህርት ቤቱ በተማሪው መብት እንደ ተማሪ እና አካል ጉዳተኛ በሌላ በኩል ደግሞ የህሙማንን ደህንነትና ህይወት አስቀምጦ በርካታ ውይይቶችን ሲያካሄዱ መቆየታቸውን አውስተዋል።
በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳብ እንዲሰጡበት በርካታ ተቋማትን ያቀፈ 11 ኮሚቴዎች ተዋቅሮ ምክክር ሲደረግ እንደነበር አንስተዋል።በዚህ ኮሚቴ የጤና ሚኒስትር፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የኮሌጁ ተማሪዎች ተወካይ፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደነበሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪ የህክምና ትምህርት ቤቱ የትምህርት ስርዓት ካሪኩለም፣ አለም አቀፍ የህክምና ትምህርት ቴክኒካል ስታንዳርዶች ላይ ምልከታ ስለመደረጉ ገልፀዋል።ለአብነትም የአሜሪካ 15 የህክምና ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ እና አሰራር ላይ ምልከታ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም አንድ ሀኪም የቆመ ልብ ማስነሳት፣ በደም ስር የሚሰጥ መድሃኒቶችን መቀጠል፣ መለስተኛ ቁስሎችን መስፋት፣ ትንፋሽ ለተቋረጠበት ሰው ኦክሲጅን መስጠት እና የማዋለድ ህክምና መስጠት የሚሉ ነገሮች የግድ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህን ተግባራት ለመፈፀም የግዴታ ሁለት እጆች የሚያስፈልጉና አለበለዚያ የሰው ህይወት አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ተናግረዋል።
በዩኒቨርስቲው የህክምና ትምህርትን ጨምሮ 8 የቅድመ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች እንደሚገኙ ያነሱት ዶክተር አንዷለም፤ ከእነዚህ ውስጥ 5ቱን የትምህርት ፕሮግራሞች ለመማር ተማሪ ቢኒያም እንደሚቸገር ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ተማሪው በፋርማሲ፣ በህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ፣ በህክምና ራዲዮሎጂ እንደ ምርጫው ትምህርቱን እንዲቀጥል ምክረ ሀሳበ መቅረቡንና ተማሪው በመረጠው ዘርፍ ትምህርቱን እንዲቀጥል እገዛ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል።
ተማሪው ወደ ተጠቀሱት የትምህርት ዘርፎች ሲዘዋወር የጤና ሳይንስ ትምህርቶች ተዛማጅነት ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር የተማራቸው ተያያዥ ትምህርቶች በሙሉ እንዲመዘገቡለት ይደረጋል ብለዋል።
ከእነዚህ ውጭ ያሉ ትምህርቶችን ብቻ እንዲማር ስምምነት ላይ መደረሱን የገለፁት ዶክተር አንዷለም፤ ያለምንም ተጨማሪ ኮርሶች የባችለር ኦፍ ሳይንስ ኢን ባዮሜዲካል ሳይንስ ዲግሪ እንዲሰጠው የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ውሳኔው ከህገ መንግስቱም ሆነ ከሌሎች አለም አቀፍ ህጎች የማይጣረስ መሆኑን ገልጸው፤ ውሳኔው ችሎታና አቅምን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለችግሩ መፈጠር በተማሪ ምልመላና ቅበላ የትምህርት ስርዓት ላይ ያለ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ችግር መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤